
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሚሊሻ አባላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት በዘላቂነት በማረጋገጥ፣ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መኾናቸውን አስታውቀዋል።
የሰላም አስከባሪ የሚሊሻ አባሉ አምሳለቃ ተረዳ ጌትነት እንደገለጹት ባለፉት ሦሥት አሥርት ዓመታት የሚሊሻ አባላት አንድነታቸውን እና ጀግንነታቸውን በማጠናከር የሰላም ማስከበር ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
አሁንም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በቁርጠኝነት እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሚሊሻ ረጅም ታሪክ ያለው እና ለሀገር አንድነት ሲዋደቅ የቆየ ኀይል መኾኑን የገለጹት ደግሞ የሚሊሻ አባሉ አምሳለቃ የኔው ውድነህ ናቸው። የቀደምት አባቶችን ጀግንነት በደም የወረሰው ይህ ኀይል ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የባሕር ዳርን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል።
አባላቱ ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሕይወታቸውን ጭምር እየገበሩ መኾኑን ጠቅሰው ለማኅበረሰቡ ደጀንነት ምሥጋና አቅርበዋል።
አምሳለቃ የኔው አክለውም “የክልሉን እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በደም እና በአጥንት ታትመን ኀላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን” ብለዋል።
ሌላኛው የሰላም አስከባሪ የሚሊሻ አባል ቸርነት አባተ በበኩላቸው የሚሊሻ አባላት ቤተሰቦቻቸውን ትተው ለሀገር ሰላም ቅድሚያ የሚሰጡ እና በተለያዩ ጊዜያት የሚጋረጡ አደጋዎችን በመቀልበስ የሀገርን አንድነት ከፍ የሚያደርጉ መኾናቸውን ገልጸዋል።
“ሚሊሻ በአንድ እጁ ልማት፣ በሌላ እጁ ጠላትን ይመክታል” ያሉት የሚሊሻ አባሉ ቸርነት አቅምን በማጠናከር የሀገርን እና የክልልን ልዕልና ለማስጠበቅ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በጥምረት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
#ሚሊሻ_ሰላምማስከበር #ባሕርዳር #Ethiopia 🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
