ብልጽግና ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በትኩረት እያለማ ነው።

6

 

ደሴ፡ ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ አስመልክቶ በጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የፓርቲውን የምርጫ ምልክት እና ዕጩ ተወዳዳሪዎችን የማስተዋወቅ መርሐ ግብር አካሄደ።

“ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት በተካሄደው በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ከተማዋን የሚወክሉ እጩዎች፣ የከተማዋ ከፍተኛ እና መካከለኛ መሪዎች እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡ ተሳታፊ ኾነዋል።

በመርሐግብሩ በዘንድሮው ምርጫ ለብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማን ወክለው የሚወዳደሩ ዕጩዎች ከሕዝቡ ጋር ትውውቅ አድርገዋል።

በፓርቲው የደሴ ከተማን በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለመወከል የሚወዳደሩት ማህተመ ኀይሌ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ትኩረት ከሰጠባቸው ተግባራት አንዱ ስፖርት መኾኑን በመግለጽ ለሀገር ገጽታ ግንባታ እና ለጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር እየዋለ ነው ብለዋል።

በዘርፉም ተጨባጭ እመርታ ተመዝግቧል ሲሉ ነው ያነሱት።

በፓርቲው ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ለወጣቶች ትኩረት በመስጠት የተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።

​በከተማዋ የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሕዝቡ ድምጽ ወሳኝ መኾኑን አቶ ሳሙኤል አንስተዋል።

ዕጩዎቹ አክለውም ለከተማዋ ዕድገት እና ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ስለመኾናቸው ገልጸዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የአካል ብቃት እንቅስቃሴው ተሳታፊ ወጣቶች ለሀገር ዕድገት እና ለወጣቱ ተጠቃሚነት ይሠራል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ከአካል ብቃት እንቅስቃሴው በተጨማሪ በክፍለ ከተሞች መካከል የገመድ ጉተታ እና ሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች ተካሂደው ለአሸናፊዎች ሽልማት ተበርክቷል።

ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየሚሊሻ አባላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሁሌም ዝግጁ ናቸው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) በጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌን የበዓለ ሲመት ላይ ተገኝተዋል።