የምርጫ ካርድ በምርጫው ዕለት የመምረጥ መብታችንን በተግባር የምናሳይበት ነው።

5

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በመጭው ግንቦት 24 ታካሂዳለች።

ዜጎችም በየደረጃው የሚተላለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ በትኩረት በመከታተል ይበጀኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

የምርጫ ካርድ ያወጡ መራጮች የምርጫ ካርዳቸውን በአግባቡ ለመጠቀም እና የሚወክላቸውን አካል ለመምረጥ በዝግጅት ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ስለሺ ሞላ የምርጫ ካርድ የመምረጥ መብታችንን በምርጫው ዕለት በተግባር የምናሳይበት ነው በማለት በካርዱ የሚመራውን ለመምረጥ እየተዘጋጀ ነው።

የምርጫ ካርድ ተራ ወረቀት ሳይኾን የዜግነት ክብር እና የዴሞክራሲያዊ መብት መገለጫ መኾኑንም ተናግሯል።

“ይኾነናል፣ ይመራናል፣ ጥያቄያችንን እና ፍላጎታችንን ይመልስልናል የምንለውንም መወሰን የምንችለው በምርጫ ካርዳችን ነው” ብሏል።

አርሶ አደር ግርማው ካሴ በበኩላቸው ቀድመው የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት አራት የምርጫ ዘመናትም በምርጫ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። ምርጫ የሚመራንን የምንመርጥበት በመኾኑ ሁሉም ካርዱን በአግባቡ መጠቀም እንደሚኖርበትም ጠቅሰዋል።

መራጮቹ አክለውም በምርጫው ዕለት ድምጽ ከመስጠት ባለፈ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ ኅይሉ ጎን ኾነው እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ

#7ኛው_ጠቅላላ #ምርጫ #Ethiopia 🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየምርምር ሥራዎች ችግር ፈቺ እንዲኾኑ መሥራት ያስፈልጋል።
Next articleየሚሊሻ አባላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ ሁሌም ዝግጁ ናቸው።