
ደብረብርሃን፡ ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ኮምፒውቴሽናል ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ ማኅበር እና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 5ኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ እና ዓመታዊ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም በቴክኖሎጂ፣ በታዳሽ ኀይል እና በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያተኮሩ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።
የደብረ ብርሃን የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማረ መለሰ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ተግባራዊ የኾኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ የኮምፒውተር ሳይንስ እና የምህንድስና ውጤቶችን በመጠቀም ዘላቂ ኀይልን እና ብሔራዊ ልማትን ለማፋጠን የሚያስችሉ የምርምር ሥራዎችን ለማኅበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የምርምር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ችግር ፈቺ እንዲኾኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ወሳኝ መኾኑን ገልጸዋል። ለዚህም የጥናት መድረኩ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በተለይም በግብርና እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ለማኅበረሰቡ ጠቃሚ የኾኑ በርካታ የምርምር ሥራዎች በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ሲሳይ ሙላቴ (ዶ.ር) አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማመንጨት የማኅበረሰቡን የዕለት ተዕለት ሕይወት ከማቅለሉም በላይ የፋብሪካዎችን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
የሚሠሩ የጥናት እና የምርምር ሥራዎችም የማኅበረሰቡን ሕይወት የሚቀይሩ እንዲኾኑ በትኩረት መሥራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
በኮንፈረንሱ ላይ የጥናት ጽሑፍ ካቀረቡ ተመራማሪዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የንግድ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ኢሽፋቅ አህመድ (ዶ.ር) አንዱ ናቸው።
በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ፈጠራ እና በታዳሽ ኀይል አጠቃቀም ላይ ያደረጉትን ጥናት አቅርበዋል። አረንጓዴ ልማት ፈጠራ እና ታዳሽ ኀይል ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት በጣሊያን ቦሎኛ ዩኒቨርሲቲ መምህር የማታው አዲስ (ዶ.ር) በውጭው ዓለም ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለመተግበር ዓለም አቀፍ መድረኮች ፋይዳቸው የላቀ መኾኑን ተናግረዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሂርፖ ሄኒሴ (ዶ.ር) የተለያዩ የምርምር ሃሳቦችን በአንድ ላይ በማቀናጀት ወደ ተግባር ለመለወጥ መድረኩ ትልቅ ግብዓት እንደሚኾን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ስንታየሁ ኀይሉ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
