
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ብልጽግና ፓርቲ በባሕር ዳር ከተማ በተሽከርካሪዎች ትርዒት የታጀበ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው “ብልጽግና ፓርቲ የተግባር ፓርቲ ነው” ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሰላምን አብዝቶ የሚፈልግ፣ ስለ ሰላም የሚተጋ፣ ስለ ሰላም የሚሠራ፣ ስለ ሰላም መሥዋዕትነትም ከፍሎ የሕዝብን ሰላም የሚያረጋግጥ ፓርቲ መኾኑን ነው የገለጹት።
ብልጽግና ዕዳን ወደ ምንዳ ለመቀየር የሚደረገውን የኢትዮጵያን ጉዞ እውን ለማድረግ የሚተጋ ፓርቲ መኾኑንም ተናግረዋል። የአፍሪካ ተምሳሌት የኾነች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አልሞ የሚሠራ ፓርቲ እንደኾነም አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ያቀደውን እና ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር የሚፈጽም መኾኑንም ተናግረዋል። ከአሁን በፊት በተሠሩት ሥራዎች የብልጽግናን የለውጥ ጉዞ በተግባር እያረጋገጠ መዝለቁን አመላክተዋል።
ለብልጽግና ስኬታማ ጉዞ ሁነኛ ማሳያ ባሕር ዳር ከተማ መኾኗንም ያነሱት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከተማዋን በብልጽግና አስተሳሰብ፣ በመደመር መንገድ ሠርተን በማልማት የሚታይ ለውጥ አምጥተናል ነው ያሉት።
“ብልጽግናን መደገፍ ሀገር ጸንታ እንድትቆይ፤ በልማት ጎዳና እንድትጓዝ፤ ሀገር ከፍ እንድትል የማድረግ ጉዳይ ነው፤ ብልጽግናን መምረጥ ሰላምን እና ልማትን መምረጥ ነው” ብለዋል።
የምርጫ ቅስቀሳው በስኬት እንዲከናወን የጸጥታ አካላት፣ መሪዎች እና የተሽከርካሪ ባለቤቶች ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #ኢትዮጵያ #ምርጫ2018 #ብልጽግና
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
