በዓባይ ተፋሰስ (ቤዚን) ላይ የሚሠሩ ሥራዎችን በቅንጅት መሥራት ይገባል።

0

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ቤዝን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት በቅንጂት የሚሠሩ የተፋሰስ ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ ሲያደርገው የነበረውን ውይይት አጠናቅቋል፡፡

ቀደም ሲል በዓባይ ተፋሰስ (ቤዚን) ላይ በሚሠሩ ሥራዎች ዕቅድ አተገባበር ውስንነቶች በጥናት ተለይተው ዕቅዱ ተከልሶ ተመክሮበታል። በቀጣይም በተፋሰሱ (ቤዚኑ) ውስጥ የተቀናጀ የንጹሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት፣ የመሥኖ ልማት፣ የተፋሰስ ልማት እና ሌሎችም ሥራዎች ላይ በቅንጅት ለመሥራት ተስማምተዋል።

የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ እና የውኃ ሀብት አሥተዳደር ሚኒስትር ድኤታ ተወካይ ሞቱማ መቃሳ የየትኛውም ሀገር ልማት መሠረት የሚያደርገው የተፋሰስ ዕቅድን መሠረት አድርጎ መኾኑን ተናግረዋል። ሁሉም ሀገራት በተፋሰስ የተከፋፈለ አቀማመጥ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ደግሞ ቁጥራቸው 12 የሚደርሱ ተፋሰሶች እንዳሏት ነው የጠቀሱት። ከዚህ መካከል ሦሥቱ ደረቅ ተፋሰሶች፣ አንደኛው የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ እና ስምንቱ የወንዝ ተፋሰስ ናቸው ብለዋል። ከስምንቱ ተፋሰሶች ዓባይ ተፋሰስ አንዱ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ዓባይ ተፋሰስ የውኃ ይዘቱ ከሁሉም በላይ ብዛት ያለው እንደኾነ ጠቅሰዋል። ለዚህም በዓባይ ተፋሰስ እና በሌሎች ተፋሰሶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት አዋጭ እንደኾነ ነው ያስገነዘቡት።

እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሁሉም ተፋሰሶች ላይ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል። አጠቃላይ የተፋሰሶች ዕቅድ መዘጋጀቱን እና ውይይት እንደተደረገበትም ተናግረዋል። አተገባበሩንም ዕቅዱ ላይ እንደተደረገው የጋራ ምክክር በጋራ ለመፈጸም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የተፋሰሶችን ዕቅድ እና ትግበራ የመከታተል እና የመደገፍ ኀላፊነት ተወስዶ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።

የሦሥቱ ክልል (አማራ፣ ኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ) የውይይቱ ተሳታፊዎች ደግሞ የዓባይ ተፋሰስ (ቤዝን) የተቀናጀ የውኃ ሀብት አሥተዳደር በተቀናጀ ኹኔታ ካልተሠራ ያለውን ሀብት በአግባቡ መያዝ እንደማይቻል ተናግረዋል። ቀደም ሲል የክትትል እና የቅንጅት ችግር በመኖሩ አተገባበሩ ላይ ውስንነት እንደነበረም ገልጸዋል። ለቀጣይ ግን የቤዚኑ ባለድርሻ አካላት ምን እና እንዴት እንደሚሠሩ ተለይተዋል ነው ያሉት።

ክልሎች በተናጠል ሲሠሩበት ከነበረው አሠራር ወጥተው በጋራ በመተጋገዝ እና በመቀናጀት ሀገር እና ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ለመሥራት ዝግጁነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየሰላም ጥሪን የተቀበሉ የቀድሞ ታጣቂዎች በአዲስ አበባ ከተማ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
Next article“ብልጽግና ፓርቲ የተግባር ፓርቲ ነው” አቶ ጎሹ እንዳላማው