
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሚሊሻ ኃይሉ ሚና ሕግ እና ሥርዓትን ማስከበር ነው ብለዋል።
ሰላምን ከማስከበር በተጨማሪ በሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችም የግንባር ቀደምትነት ሚናውን እየተወጣ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን እየተወጣ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የምርጫውን ሂደት ደህንነት መጠበቅ እና ምቹ ሁኔታን መፍጠር የሚሊሻ ኃይሉ ቀዳሚ አጀንዳ ነው ብለዋል። እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በምርጫ ቦርድ መመሪያ መሠረት ግንዛቤ ተፈጥሮለት ወደ ሥራ መግባቱን ነው የተናገሩት።
እስከ አሁን ባለው ሂደትም መራጮች በነጻነት ተመዝግበው እና ካርዳቸውን እንዲወስዱ በመጠበቅ ረገድ ተልዕኮውን ሲወጣ መቆየቱን አንስተዋል።
የምርጫ ቁሳቁሶች፣ የምርጫ ጣቢያዎች እና አሥፈጻሚዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የሚሊሻ ኃይሉ በየመንደሩ ከሕዝቡ ጋር አብሮ የሚኖር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት እና የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ለማኅበረሰቡ የቀረበ ኃይል መኾኑን ተናግረዋል።
ለምርጫው ስኬታማነት የምርጫ ሂደቱን በያለበት አካባቢ ኾኖ እንዲጠብቅም መመሪያ ተሰጥቶበት በየደረጃው በጥብቅ ስነ ምግባር እየተመራ መኾኑን ገልጸዋል።
ሕዝቡም በየአካባቢው አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ ኃይሉ በፍጥነት በመጠቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የጸጥታ ኃይሉም የተጣለበትን ኀላፊነት በብቃት እንዲወጣ አሳስበዋል።
#አሚኮ #ምርጫ2018 #ሚሊሻ #ሰላም
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
