
ፍኖተሰላም፡ ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ሚሊሻ መምሪያ ”ሚሊሻ የጥንት የኢትዮጵያ አርበኞች የትውልድ ቅብብሎሽ” በሚል መሪ መልዕክት 30ኛ ዓመት የሚሊሻ ምሥረታ በዓልን አክብሯል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ ሚሊሻ በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ፤ ሀገር ሲደፈር ደግሞ ጠላትን የሚፋለም የቁርጥ ቀን ኀይል ነው ብለዋል።
ሰላም እንዲሰፍን እና ምርጫው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ የታሪካዊ ጠላቶችን ሴራ ማምከን እንደሚገባም ጠቁመዋል። ሚሊሻው 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የሚሊሻ ኀይሉን በተገቢው መንገድ ለማደራጀት ዞኑ አስፈላጊ ድጋፎች እንደሚያደርግም ነው የጠቆሙት።
የዞኑ ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ መንግሥቱ ተስፋየ የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሠሩ ኀይሎችን የሚሊሻ ኀይሉ ከሌሎች የጸጥታ ኀይሎች ጋር በመቀናጀት ዕኩይ ዓላማቸውን ለማክሸፍ እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በክልሉ የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት የሚሊሻ ኀይሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራ ይገኛል ነው ያሉት።
ወደ ኅብረተሰቡ በመግባት ሰላምን ለማወክ የሚጥሩ ኀይሎችን በመለየት የሕግ ማስከበር ሥራን እያከናወኑ መኾናቸውንም አመላክተዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ የሚሊሻ አባላት በበኩላቸው ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በሠሩት ሥራ ሰላሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። ቀጣይም የሰላም ማስከበር ሥራውን በማጠናከር የሰላሙ ሁኔታ እንዲረጋጋ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም አረጋግጠዋል። 7ኛው ጠቅላላ ምርጫም በስኬት እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
#የ7ኛው_ ጠቅላላ_ምርጫ_አማራ_ክልል #Ethiopia 🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
