
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በምዕራብ እዝ ውስጥ ባሉ ክፍለ ጦሮች ተገኝተው የሠራዊቱን ዝግጁነት ተመልክተዋል።
በግዳጅ ቀጣናው መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ የምዕራብ እዝ የሠራዊት አባላት በሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት ላይ የተደቀኑ ፈተናዎችን ለመቀልበስ አሥፈላጊውን ሁሉ መክፈላቸውን ገልጸዋል።
ምዕራብ እዝ በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ ሲጋረጥባት በግንባር ቀደምትነት ተሰልፎ መስዋዕትነት የከፈለ እዝ ነው ብለዋል።
በሕጋዊ መንገድ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በአፈሙዝ ለማስወገድ እና የሕዝብን ሠላም ለማደፍረስ የሚደረግ ማናቸውም ሙከራ ሠራዊታችን እያለ አይሳካም ነው ያሉት። ለሕዝብ የሚጠቅም አማራጭ ሃሳብ ያለው ማንኛውም አካል ሕጋዊ እና ሠላማዊ መንገዶችን ተጠቅሞ ምኞቱን ለማሳካት መሥራት እንደሚችል እና የዘመኑ ብቸኛ አማራጭም ይህ ብቻ እንደኾነ አስገንዝበዋል።
የምዕራብ እዝ አባላት ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅርና ለቃለ መሃላቸው ታማኝ መኾናቸው ለሌሎች የሠራዊቱ ክፍሎች አርአያ እንደሚኾን ገልጸዋል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታም ዕዙ ማንኛውንም የውጭም ኾነ የውስጥ የጸጥታ ስጋቶችን ለመመከት በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እዙ በሰው ኃይል፣ በሥልጠና እና በስነ ልቦና የታነጸ በመኾኑ ማንኛውንም የጠላት ኃይል የመደምሰስ አቅም እንዳለው እና መቺ ኀይል መኾኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ምዕራብ እዝ ትናንት ሀገርን ታድጓል፤ ዛሬም የሀገር አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል ያሉት ጄኔራል አበባው ነገም ማንኛውንም ሉዓላዊነትን የሚነካ ጥቃት የማያዳግም ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ የኾነ እዝ መኾኑን ጠቁመዋል።
ከሀገር መከለካያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አማረ ባህታ ዕዙ በማንኛውም ሰዓት የሚሰጠውን ግዳጅ ለመወጣት ከምንግዜውም በላይ በአስተማማኝ የዝግጁነት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
