
ፍኖተ ሰላም፡ ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕሳብ ጎጃም ዞን የጃቢጠህናን ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች በተገኙበት ለ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የምርጫ ቅስቀሳ እና የድጋፍ ሰልፍ በማንኩሳ ከተማ አካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ የቻለ ይርጋ ብልፅግና ፓርቲ በወረዳው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ ፓርቲ መኾኑን ተናግረዋል።
በተለይ ሰው ተኮር ተግባራትን በማከናወን በሰፊው እየሠራ ያለ ፓርቲ ስለመኾኑም አስረድተዋል።
በወረዳው ምርጫው በፍትሐዊነት፣ በሰላማዊ እና ቅቡልነትን በተመላ መንገድ እንዲጠናቀቅ በሰፊው እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማከናወን የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ፓርቲ መኾኑን በፓርቲው የምዕራብ ጎጃም ዞን ቅርጫፍ ጽሕፈት የኢንስፔክሽን እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ኀላፊ ክብረት ሞላ ተናግረዋል።
ምርጫ የሥልጡን ዜጋ መገለጫ ነውም ብለዋል። ከመጠፋፋት በመውጣት በምርጫው ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መከተል እንደሚያስፈልግም ነው ያስረዱት።
ብልፅግና ፓርቲ ከዚህ በፊት የነበሩ የፓለቲካ ቁርሾዎችን ለመፍታት በተጨባጭ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
በተለይ ሰላማዊ የፓለቲካ አካሄዶችን ለማሳለጥ በልዩ ትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ የሕዝባዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች እንዳሉት ምርጫ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመኾኑ በመጪው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
