
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዓባይ ቤዝን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት የቤዝን ሥራዎች ላይ ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት እያደረገ ነው፡፡
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብሔራዊ የተቀናጀ የውኃ ሃብት አሥተዳደር አሥተባባሪ ብዙነህ አስፋው (ዶ.ር) ከዚህ በፊት የውኃ ሃብትን ዘላቂ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ ለመጠቀም ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል። ትግበራው ላይ ግን ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
ዓባይ ቤዝን ከክልል ባሻገር ከሀገር ውጭም ብዙ ፍላጎት ያለበት ነው ያሉት አሥተባባሪው እንደ ሀገር የሚሠሩ ሥራዎች በጋራ ታቅደው በመተጋገዝ እና በትብብር ሊተገበሩ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።
ይህ ሲኾን እየጠፉ ያሉ ከውኃ ጋር የተያያዙ ሃብቶችን ወደ ነበሩበት የመመለስ እና በፍትሐዊነት የመጠቀም ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
የአማራ ክልል ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ኢንጅነር ዳኝነት ፈንታ (ዶ.ር) በኢትዮጵያ ብቻ የዓባይ ወንዝ ዓመታዋ የውኃ ሃብት አማካይ ምጣኔ ከ45 እስከ 50 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚገመት ትልቅ ሃብት እንዳለ ተናግረዋል። ከኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አኳያ እስከ 45 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው መኾኑንም ገልጸዋል። ለመስኖ መሠረተ ልማትም ሰፊ ዕድል ያለው ነው ብለዋል።
ዓባይ ቤዝን ለሀገርም ኾነ ለክልሎች ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ትልቅ ስለኾነ ሃብቱን ሳይንሳዊ በኾነ ዘዴ ማጥናት፣ ማቀድ እና ፍትሐዊ በኾነ መንገድ በአግባቡ ማሥተዳደር አስፈላጊ እንደኾነም አንስተዋል።
የዓባይ ቤዝን አሥተዳደር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዮሐንስ መላክ በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የኾነ የዓባይ ቤዝን ሃብት አጠቃቀም በዘላቂነት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ቀደም ሲል ታቅደው የነበሩ የዓባይ ቤዝን ሥራዎች ሙሉ በሙሉ አለመከናወናቸውን ነው የጠቀሱት።
ይህ ሲኾን ባዮ ዳይቨርሲቲ ይጎዳል፤ ይህም የሥነ ምህዳር መዛባትን ያስከትላል ብለዋል። ይህ እንዳይኾን በጋራ እና በትብብር መሥራት እንደሚጠይቅ ነው የገለጹት።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ቀደም የዓባይ ቤዝን ልማት ሥራዎች ከተሠሩ በኋለ የሚደረግ ጥበቃ እና እንክብካቤ ውስንነት እንደነበረበት ተናግረዋል።
የሚሠሩ ልማቶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ደግሞ ተቀናጅቶ ምላሽ መስጠት አስፈላጊ በመኾኑ በቀጣይ በትኩረት ለመሥራት ጥረት እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
