የሚሊሻ አባላቱ ከልማት ጎን ለጎን ለሀገር ሰላም ዋጋ ከፍለዋል።

6
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ መምሪያ 30ኛ ዓመት የሚሊሻ ምስረታ በዓልን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የሚሊሻ አባላት በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም አኩሪ ድል ያስመዘገቡ የሀገር ልጆች መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሕዝቡን ከተዛባ ትርክት በመመለስ እና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር የድርሻቸውን ለመወጣት ጥረት ያደረጉ መኾናቸውንም አንስተዋል። በቀጣይም የሰላም ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ የሚሊሻ አባላቱ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከልማት ጎን ለጎን ለሀገር ሉዓላዊነት ዋጋ መክፈላቸውን ገልጸዋል።
ሚሊሻ ከማኅበረሰቡ የወጣ የሰላም ምሰሶ እና የሰላማችን ዘብ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ እንደ ወርቅ በእሳት የተፈተነ ጠንካራ የሚሊሻ አባላት መገንባት ተችሏል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የሚሊሻ አባላት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው ሀገርን ከመፍረስ ታድገዋል ብለዋል።
የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት እና ወቅታዊ የጸጥታ ችግርን በመቀልበስ ሰላምን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ ሚሊሻው እና መላው የጸጥታ ኃይል ሰላምን የማረጋገጥ ሚናውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ ገበያው አዳነ ሚሊሻው ለሀገር ሰላም ደም እና አጥንቱን እየከፈለ መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መሪዎች የሚሊሻ ኃይሉን በቴክኒክ እና ታክቲክ የበቃ እንዲኾን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

See less
Previous articleሚዲያዎች ስለ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ ማድረስ አለባቸው።
Next articleየዓባይ ተፋሰስ ሃብት፤ ከባሕላዊ አጠቃቀም ወደ ሳይንሳዊ እና የተቀናጀ ልማት