ሚዲያዎች ስለ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ ማድረስ አለባቸው።

10
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢፌዴሪ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር እና የንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በተመለከተ ከሚዲያ ባለሙያወች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ኤርሚያስ ተክሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዜጎች በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ወቅት የሚገጥሟቸውን እንግልቶች ለመቅረፍ የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በዘርፉ ይታዩ የነበሩ የሕገ ወጥ ስምሪቶች ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አዲስ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ መግባቱንም ተናግረዋል። ይህ አሠራር ዜጎች መብታቸው፣ ክብራቸው እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በውጭ ሀገር እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
የሚዲያ አካላት ስለ ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ትክክለኛ መረጃዎችን ለሕዝቡ በማድረስ ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መኾኑን ያነሱት ደግሞ የንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ መሥራች እና ሥራ አሥኪያጅ ዳንኤል መለሰ ናቸው።
መደበኛ ያልኾነ ስደት በሀገር እና በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደኾነም ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መደበኛ (ሕጋዊ) የኾነ የሥራ ስምሪትን ለማጠናከር የሚሠሩ መልካም ሥራዎችን ሚዲያዎች የማሳየት ኀላፊነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 1389/2018 መሠረት ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ በውጭ ሀገር ለሥራ እንዲሰማሩ ከሀገራት ጋር እየሠራ እንደኾነ የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ዴስክ ኀላፊ በዛወርቅ ከተማ ናቸው።
ሚዲያዎች ትክክለኛውን መረጃ ለዜጎች በማድረስ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less
Previous articleጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ የኃይል አቅርቦት ችግሩን ቀርፎ ወደማምረት ሊገባ ነው።
Next articleየሚሊሻ አባላቱ ከልማት ጎን ለጎን ለሀገር ሰላም ዋጋ ከፍለዋል።