
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ በሰሜን ምዕራብ እዝ የግዳጅ ቀጣና ተገኝተው የሠራዊቱን የዝግጁነት ደረጃ ተመልክተዋል።
በግዳጅ ቀጣናው መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ የሰሜን ምዕራብ እዝ ከየትኛውም አቅጣጫ ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን መከላከል በሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
እዙ ከታሪካዊ ጠላቶችም ይሁን ከባንዳዎች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን መመከት እና መደምሰስ በሚያስችለው የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ሰሜን ምዕራብ እዝ የተሰጠውን ግዳጅ በላቀ ጀግንነት እየፈፀመ የመጣ የተቋማችን አስተማማኝ እዝ ነው ብለዋል። እዙ የሕወሃትን ሀገር የማፍረስ ተከታታይ ወረራ በመመከት ሀገርን በማፅናት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ አንስተዋል።
ሰሜን ምዕራብ እዝ በአማራ ክልል ግጭት እና ሁከት ለመፍጠር በተንቀሳቀሰው የሀገር ውስጥ ባንዳ በኾነው ፅንፈኛው ቡድን ላይ ጠንካራ ምት በማሳረፍ ያሰበውን ኢትዮጵያን የማጥፋት ሴራ አክሽፏል ነው ያሉት። ፅንፈኛው ቅስሙ እንዲሰበር እና እጅ እንዲሰጥ በማድረግ ወገን የኮራበት፤ ጠላት ያፈረበትን ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል ብለዋል።
እናንተ የአባቶቻችሁን የጀግንነት ታሪክ እና አደራ ተቀብላችሁ ኢትዮጵያን ለመጨው ትውልድ ለማስረከብ ላደረጋችሁት እና በቀጣይም ለምታደርጉት ተጋድሎ ኢትዮጵያ እና ተቋሙ ይኮሩባችኋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ማደግ እና መለወጥ ስጋት የኾነባቸው ታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች በቀጥታ እና በውስጥ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ከልማቷ ወደ ኋላ ለማስቀረት ሌት ተቀን ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ምንጊዜም የኢትዮጵያ አለኝታ የኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠላቶችን አንገት በማስደፋት ኢትዮጵያ ወደ እድገት የምደታረገው ጉዞ እንዲፋጠን፣ የሕዝቦቿን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷልም ብለዋል።
የሰሜን ምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እዙ ከተቋሙ የተሰጡትን ተደራራቢ ግዳጆች ተቀብሎ በፅናትና በቁርጠኝነት መፈጸሙን ገልጸዋል።
ከሀገር መከለካያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ለቀጣይ ግዳጅ እና ተልዕኮም ዝግጁነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የላቀ ነው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
See less
