የጣናዋ ንግሥት በአዲስ ገጽታ !

4
🏙️
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዘንባባ የደመቀችው እና በዓባይ የታጀበችው የጣናዋ ንግሥት ባሕር ዳር ከተማ ውበቷን በሚያጎላ የኮሪደር ልማት እያሸበረቀች ነው።
ለወትሮው ታይታ የማትሰለቸው፤ አድራ አዲስ የኾነችዋ ውቢቷ ባሕር ዳር ዛሬም መዋቧን ቀጥላለች። የኮሪደር ልማቱ ከተማዋ ያላትን ተፈጥሯዊ ጸጋ ከዘመናዊ የከተማ እድገት ጋር ያቀናጀ ነው።
እስከ አሁን በተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎች ሰፊ የእግረኛ መንገዶች፤ የብስክሌት መጋለቢያዎች፤ አረንጓዴ ፓርኮች፤ የውኃ እና የመንገድ ዳርቻ መዝናኛዎች ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን ሰጥተዋታል።
ከተማዋ በአረንጓዴ ተውባ፤ በጌጠኛ መብራቶች ተንቆጥቁጣ ወደ ሳቢ እና ማራኪ ገጽታ እየተቀየረች ነው።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ከተማዋ በሁለንተናዊ የልማት ጎዳና ላይ መኾኗን ገልጸዋል።
የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
እስከ አሁን በተሠራው የኮሪደር ልማት ሥራ:-
👉 የጣና ዳርቻ በበርካታ ቦታዎች ተከፍቷል፤
👉 ከጊዮርጊስ -ዲፖ፣ ከጊዮርጊስ እስከ አጂፕ ያለው የኮሪደር ልማት በስኬት ተከናውኗል፤
👉 ከአልማ- ዋተር ፍሮንት ደረጃውን የጠበቀ አዲስ አስፋልት መንገድ ተገንብቶ ተጠናቅቋል፤
👉 ከጊዮርጊስ -ፓፒረስ፣ ከዲፓ -ገጠር መንገድም በፍጥነት እየተሠራ ነው።
👉 ከገጠር መንገድ እስከ በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስም በከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት እየተገነባ ነው።
👉 የተገነቡት መናፈሻ እና የዓደባባይ ስፍራዎችም የነዋሪዎች እንቅስቃሴ በማሳለጥ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ፋይዳቸው የጎላ ነው።
እስከ አሁን የተከናወኑት የኮሪደር ልማት ሥራዎችም ውጤታማ መኾናቸውን ነው የገለጹት። ሦስተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
ከተማዋን ለቱሪዝም ምቹ እንድትኾን የተጀመሩ ሆቴሎች እንዲጠናቀቁ እና አዳዲስ ሆቴሎች እንዲገነቡም በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
🏙️“ስማርት ባሕር ዳር ፕሮጀክትን” ወደ ተግባር በማስገባት ዘመናዊ ከተማ የመፍጠር ጉዟችን ይቀጥላል ነው ያሉት።
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

See less
Previous articleበባሕር ዳር ከተማ ውስጥ የሚያለሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግሮች ለመፍታት እየተሠራ ነው።
Next articleምርጫን ለማደናቀፍ መሞከር ከፍተኛ የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል።