
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምርጫን ማወክም ኾነ ለማደናቀፍ መሞከር የሕግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በሕግ ተደንግጓል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ፍትሕ መምሪያ የወንጀል አቃቢ ሕግ ባሙያው ሰለሞን ምስጋናው የኢትዮጵያ ምርጫ፤ የፖለቲካ ምዝገባ እና ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና ይሄን ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 1394/2017 አንቀጽ 157፣158 እና 159 የተከለከሉትን ለመጣስ መሞከር ተጠያቂ እንደሚያደረግ በግልጽ አስፍሯል ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲን ዓላማ በኃይል ወይም በማስፈራራት ለማስረጽ ማንኛውንም ሰው ወይም ቡድን ማደራጀት የተከለከለ መኾኑን ገልጸዋል።
ሰዎችን በግድ መመልመል እና ለዚሁ ድርጊት እርዳታ ማድረግም ኾነ መተባበር አግባብ ባለው ሕግ የሚያስቀጣ ተግባር እንደኾነ ነው የገለጹት።
በዋናነት ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ ውጭ የምርጫ ሰነዶችን እና ቁሳቁሶችን ማሳተም፣ ማባዛት፣ መፈብረክ፣ መያዝ፣ በድምፅ መስጫ ዕለት በድምፅ መስጫ ጣቢያ አካባቢ ድምፅ ከመስጠት ውጭ ሌላ ማንኛውንም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስቀጣል ነው ያሉት።
በተከለከለ ጊዜ የምርጫን ውጤት ማተም ወይም ማዛባት ከ80 ሺህ ብር እስከ 100 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት የሚያስቀጣ መኾኑ በወንጀል ሕጉ ተመላክቷል ብለዋል።
ጥላቻን ወይም ፍርሀትን የሚቀሰቅስ ወይም በምርጫው ውጤት ላይ ጫና የሚፈጥር የሐሰት መረጃ አሳትሞ ማሠራጨት ወይም ለማሠራጨት መሞከር በገንዘብ እና በእስራት እንደሚያስቀጣም አንስተዋል።
ይህ ቅጣትም ከ30 ሺህ እስከ 50 ሺህ የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እና ከስድስት ወር በማያንስ፤ ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል መኾኑን አብራርተዋል።
የምርጫ ቦርዱ በሚሰጠው ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ላይ ተገቢ ያልኾነ ተጽዕኖ ለማሳደር የኃይል ተግባር መፈጸም ከብር 30 ሺህ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ያስቀጣል ነው ያሉት።
የድምፅ ውጤት እስከሚገለጽበት ቀን ድረስ የማንኛውንም እጩ ተወዳዳሪ የምርጫ ማስታወቂያን ማበላሸት ከአንድ ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚያስቀጣም ተመላክቷል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሙላት ክንፉ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
