
አዲስ አበባ፡ ሚያዚያ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እስከ 6 ዓመት ዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናት አዕምሯዊ፣ አካላዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ጤንነትን ለመገንባት የሚያስችል የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ጉባኤ ከግንቦት 3/2018 ዓ.ም እስከ ግንቦት 5/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ጉባኤው “የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ሥርዓት ለውጥ የግንባር ቀደምትነት ሚና፤ ከአካባቢያዊ ሞዴሎች ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ” በሚል መሪ መልዕክት እንደሚካሄድ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ከበደ ወርቁ (ዶ.ር) በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የአፍሪካ ቀዳማይ ልጅነት ልማት ማዕከል በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሕፃናትን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በምርምር እና በሳይንሳዊ ሥልጠናዎች ላይ የተመሠረተ መርሐግብር ቀርጾ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።
ማዕከሉ በዋናነትም ተጋላጭ ቤተሰቦችን በመደገፍ ላይ ያተኩራል። የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስመዘገቡትን ስኬታማ ተሞክሮ እንደ መነሻም ይወስዳል።
የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የተሻለ የአሥተዳደግ ሥርዓት ለመፍጠር ይሠራል። የተመዘገቡ ስኬቶች እና የዜጎች ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ነው የተባለው።
እስካሁን ባለው ሂደት በተከናወኑ የትምህርት ቤት ምገባ፣ ምቹ የመጫወቻ ስፍራዎች ግንባታ፣ የሕፃናት ማቆያ አገልግሎት እንዲሁም በቤት ለቤት ድጋፎች ከ350 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉም ተብራርቷል። ኢትዮጵያ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ያካበተችውን ውጤታማ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት ለማካፈል እና የሌሎችንም ልምድ ለመውሰድ ጉባኤው ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በመጭው ግንቦት በሚካሄደው በዚህ ታላቅ ጉባኤ ላይም ከሀገር ውስጥ፣ ከአፍሪካ እና ከተለያዩ አህጉራት የተወጣጡ ከ350 በላይ ተሳታፊዎች ይታደማሉ።
በፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የአሠራር ሥርዓት እና የሰው ኀይል ግንባታ እንዲሁም በፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ሰፊ ውይይቶች እና የምስክርነት መድረኮችም ይካሄዳሉ ተብሏል።
ቀዳማይ ልጅነት ለአንድ ሕፃን የነገ ማንነት መሠረት በመኾኑ በዘርፉ የሚከናወኑ መሰል ኢንቨስትመንቶች ለሀገር እና ለአህጉር ብልጽግና ወሳኝ ድርሻ እንዳላቸውም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ሰላማዊት ነጋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
