
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቱሪዝም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ካልታገዘ በዘርፉ ዕድገት እና ተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።
በሀገር የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ የመረጃ ተደራሽነት አለመኖር፣ የገቢ መጠን መቀነስ፣ ዝቅተኛ ተወዳዳሪነት እና የአገልግሎት ጥራት ችግር እንዲከሰት ያደርጋል። ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ገቢ እንዲቀንስ ምክንያት ይኾናል።
ከቱሪዝም የሚገኝን ገቢ ለማሳደግ እና ጎብኝዎችን ለመሳብ ደግሞ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን በዲጂታል ማዘመን ግድ ይላል።
የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዲጂታል ለማድረግ እየሠራ ይገኛል። በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ ሢሠራ እንደነበር ተናግረዋል።
ተቋሙ በቅርቡ የተቀናጀ የቱሪዝም አሥተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ወደ ሥራ ገብቷል። አገልግሎቱን ዲጂታል በማድረግ በፖርታል ሲስተም እና በሞባይል መተግበሪያ ጎብኝዎች ቋሚ መረጃን እንዲያገኙ ወደ ሥራ መገባቱን አንስተዋል።
ፖርታል እና የሞባይል መተግበሪያው ጎብኝዎች ወደ ሀገሪቱ እና ወደ ክልሉ ከመምጣታቸው በፊት ሙሉ መረጃ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
በክልሉ በ2018 ዓ.ም በዘጠኝ ወራት ከ42 ሺህ 800 በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች እና ከ15 ሚሊዮን 953 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎች መጎብኘታቸውን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ጎብኝዎች ከ12 ቢሊዮን 324 ሚሊዮን 564 ሺህ ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
