ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መርከቦችን አጅቦ የማውጣቱ ዘመቻ ለጊዜው እንዲቆም አዘዙ።

5

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዶናልድ ትራምፕ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መርከቦችን አጅቦ የማውጣቱ ዘመቻ ለጊዜው እንዲቆም አዝዘዋል።

የአሜሪካ የጦር መርከቦች እና የንግድ መርከቦችን በወሽመጡ ውስጥ ታጅበው እንዲያልፉ የሚያደርገው ሥራ በድንገት እንዲቋረጥ ተደርጓል። ዓላማው ደግሞ ከኢራን ጋር ለሚደረገው የሰላም ስምምነት ዕድል ለመስጠት እንደኾነ ቴሌግራፍ ዘግቧል።

ትራምፕ በወሽመጡ ላይ የተጣለው ከበባ እንደቀጠለ ኾኖ የሰላም ስምምነቱን ለማርቀቅ እና ለማጽደቅ እንዲቻል የጥበቃ ዘመቻው ለጥቂት ጊዜ እንዲቆም መወሰናቸው ተመላክቷል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት በሰላም ድርድሩ ላይ ትልቅ መሻሻል ታይቷል በሚል ቢኾንም ውሳኔው የመጣው ኢራን በአሜሪካ የጦር መርከቦች ላይ ሚሳይል ተኩሳ በነበረበት እና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይም የድሮን ጥቃት በሰነዘረችበት ወቅት ነው ብሏል ዘገባው።

በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ ከበባ የኢራንን የነዳጅ ሽያጭ በእጅጉ ጎድቷል። የዓለም የነዳጅ ዋጋም እንዲጨምር አድርጓል። ይህም የኢራንን 90 በመቶ ነዳጅ በምትገዛው ቻይና ላይ ጫና ፈጥሯል ነው የተባለው።

ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ቤጂንግ በማቅናት ቻይና በኢራን ላይ ተጽዕኖ እንድታሳድር ግፊት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢራን ግን አሁንም በወሽመጡ ላይ ለሚንቀሳቀሱ መርከቦች ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እየሰጠች ትገኛለች። ትራፕ ደግሞ ኢራን ነጭ ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ እጅ መስጠት እና የኒውክሌር ፕሮግራሟን የሚያስቆም ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባት አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleከታሪፍ በላይ ከማኅበረሰቡ የተወሰደን ብር እያስመለስን ነው።
Next article“ፍርድ ቤቶች በቀበሌ ቤቶች ይዞታ ላይ የመዳኘት ሥልጣን የላቸውም” የፌዴሬሽን ምክር ቤት