
አዲስ አበባ፡ ሚያዚያ 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የፍርድ ቤቶች ሚና፣ ተግዳሮት እና መፍትሔው” በሚል መሪ መልዕክት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች፣ ከከፍተኛ መሪዎች እና ከሕግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ምክር ቤቱ ሀገራዊ አደጋዎችን የሚታደጉ እና የግለሰቦችን እንዲሁም የቡድኖችን መብት የሚያስከብሩ በርካታ የሕገ-መንግሥት ትርጓሜዎችን ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰዋል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፍርድ ቤቶች ከመንግሥት የረጅም ጊዜ ይዞታዎች እና ቤቶች ጋር በተያያዘ የምክር ቤቱን ውሳኔ ያላከበሩ ብያኔዎችን እየሰጡ መኾኑን ጠቁመዋል።
አፈ-ጉባኤው እንደገለጹት፣ ፍርድ ቤቶች በየደረጃው የሚቀርቡላቸውን “የቀበሌ ቤቶች” ተብለው የሚጠሩ የረጅም ጊዜ የመንግሥት ይዞታዎች ክርክር እና አቤቱታ የመዳኘት ሥልጣን የላቸውም። አፈ ጉባኤው ዋና ዋና ምክንያቶችን ሲያብራሩ እንዳሉት ምክር ቤቱ ሰኔ 25 ቀን 2016 ዓ.ም በመዝገብ ቁጥር 113/16 በሰጠው ውሳኔ፤ ለረጅም ጊዜ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ቤቶች “ከአዋጅ ውጭ ተይዘዋል” የሚል ክርክር ሥልጣን ባለው አካል እስካልተረጋገጠ ድረስ፣ ቤቱ የመንግሥት እንደኾነ ተደርጎ እንደሚወሰድ አስገዳጅ ትርጓሜ ሰጥቷል።
በአዋጅ ቁጥር 47/67 መሠረት የመንግሥት የተደረጉ የትርፍ ቤቶች ክርክርን የማየት ሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 110/87 መሠረት ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የተሰጠ እንጂ ለፍርድ ቤቶች አለመኾኑ ተብራርቷል። ይህ መብትም በአዋጅ ቁጥር 572/2000 ዓ.ም በይርጋ የታገደ መኾኑ ተጠቅሷል።
በውይይቱ በቀረበው ጽሑፉ ላይ እንደተመላከተው፣ ፍርድ ቤቶች ቅፅ 003 እና 004 የተባሉ ሰነዶችን እንደ ብቸኛ የባለቤትነት ማስረጃ አድርገው መውሰዳቸው ተገቢ እንዳልኾነ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት የረጅም ጊዜ የመንግሥት ቤቶችን ይዞታ፣ ከአዋጅ ውጭ የተወረሱ ቤቶችን የማየት ሥልጣን፣ የማስረዳት ሸክምን እና የቅፅ አገልግሎትን በተመለከተ፣ የሰጣቸው ውሳኔዎች በመጨረሻ ውሳኔነት እንዲጠቀሙባቸው ጥሪ ቀርቧል።
በአዋጅ ቁጥር 1261/2011 መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጣቸው ውሳኔዎች የመጨረሻ እና እንደ ሕገ-መንግሥቱ እኩል የሚታዩ ናቸው። በመኾኑም ከዚህ ትርጓሜ ጋር የሚቃረኑ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9/1 መሠረት ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው አፈ-ጉባኤው አስገንዝበዋል።
ውይይቱ በፍትሕ አካላት መካከል ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር እና የሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜዎችን ወጥነት ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ቀጥሎ እየተካሄደ ይገኛል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
#የፍትሕ_ሥርዓት #Ethiopia 🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
