“የሀገር ፍቅር እና ጽናትን ከአባቶቻችን እንውረስ” ልጅ ዳንኤል ጆቴ

9

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 (አሚኮ) ጣሊያን የፈጸመችውን ወረራ እና አርበኞች ለነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚዘክረው የአርበኞች የድል በዓል ለ85ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የአርበኞችን ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ እና ከታሪኩ በመማር ለሀገራዊ ብልጽግና መሥራት ይገባል ብለዋል።

የቀድሞው ትውልድ በዱር በገደል ተሠማርቶ ለጠላት ሳይንበረከክ እና በቂ ስንቅ እና ትጥቅ ሳይኖረው ሀገሩን ከወራሪዎች በመጠበቅ ታላቅ ታሪክ መሥራቱንም ገልጸዋል። ይህ ታላቅ ገድል አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ ትምህርት እንደሚሰጥም አስረድተዋል።

አሁን ያለው ትውልድ ከቀድሞው ትውልድ “የሀገር ፍቅር እና ጽናትን” በመማር በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚ፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ መስኮች አዳዲስ ጀግኖችን እና አርበኞችን መፍጠር እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።

የአርበኞች ቀን በየዓመቱ የሚከበረው የቀድሞውን ታሪክ ለማስታወስ ብቻ እንዳልኾነ እና ይልቁንም ትውልዱ ዛሬ ላይ ቆሞ ለነገው የሀገሪቱ ብልጽግና እንዲያስብ ለማድረግ ጭምር ነው ብለዋል።

ታሪክ የመዘከሩ ዓላማ ትውልዱ ካለፈው ታሪክ በመማር ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያሸጋግር ለማበረታታት መኾኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያንን የቆየ የአብሮነት እሴት እና የአባቶቻችን ታሪክ ማክበር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር ለጸጥታ አባላት የቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ።