
ደሴ: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር በቤት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ የጸጥታ አባላት የቤት መሥሪያ ቦታ አስረክቧል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ የጸጥታ ኃይሉ የከተማዋን እና የሕዝቡን ሰላም በመጠበቅ ዋጋ ከፍሏል ብለዋል። በጸጥታ ኃይላችን ላብ እና ደም ከተማችንን ከጽንፈኞች በመጠበቅ ሰላም አድርገናል ነው ያሉት። “ይህ የልፋታችሁ ውጤት ነውና ይገባችኋል” ብለዋቸዋል።
መንግሥት በቤት ልማት ዘርፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው
የጸጥታ ኃይሉም በተመሳሳይ በአነስተኛ ክፍያ የቤት ባለቤት እንዲኾን ለማድረግ መሠራቱን አንስተዋል።
ዛሬ ለ125 የቤት ማኅበራት የቦታ ርክክብ መደረጉን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ፓሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ (ዶ.ር) የክልላችን የጸጥታ ኃይል ሀገርን ከመፍረስ የታደገ ባለውለታ ነው ብለዋል።
አባላቱ የቤት ባለቤት እንዲኾኑ የክልሉ መንግሥት እና የክልሉ ምክር ቤት በልዩ ሁኔታ የሰጡት ትኩረት የሚመሰገን እንደኾነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) የጸጥታ መዋቅሩ የሚከፍለውን ዋጋ ታሳቢ በማድረግ የክልሉ መንግሥት መመሪያ በማውጣት የቦታ እና የቤት ባለቤት እንዲኾኑ መሥራቱን ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ከ2 ሺህ 900 በላይ ለሚኾኑ የጸጥታ ኃይሎች የቤት መሥሪያ ቦታ ማስረከቡ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
የጸጥታ ኃይሎቻችን የጠላትን አጀንዳ በማክሸፍ ሀገር ገንብታችኋል፤ ለትውልድ የሚሻገር ገድል ተወጥታችኋልና የጀመራችሁትን ሥራ አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ብለዋል። የክልሉ መንግሥት በቀጣይም ከጎናችሁ ኾኖ አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ተመስገን አሰፋ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
