ከታሪፍ በላይ ከማኅበረሰቡ የተወሰደን ብር እያስመለስን ነው።

11

ባሕርዳር፡ ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ በተፈጠረ የነዳጅ ዋጋ መጨር እና የቁጠባ ሥራ ምክንያት በመንግሥት በኩል መጠነኛ የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጎ ነበር።

ይህንን ምክንያት በማድረግ በርካታ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ያለ አግባብ ሥሥት እጥፍ እና ከዛ በላይ ገንዘብ በመጨመራቸው ማኅበረሰቡ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየተዳረገ ይገኛል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያም ይህን ችግር ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በሥሩ ከሚገኙ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች እና አጋር አካላት ጋር ምክክር በማድረግ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ደሳለኝ አበራ እንደ ሀገር የተፈጠረውን የነዳጅ አቅርቦት ውስንነት እና መጠነኛ የትራንስፖርት ጭማሪ እንደ ምቹ ኹኔታ በመጠቀም የሚደረግን የትራንስፖርት ጭማሪ ለማኅበረሰቡ የማስመለስ ተግባር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ከዞን ባሻገር ከአጎራባች ዞኖች ጋርም በመመካከር በቅንጅት ለመሥራት ጥራት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም በሰባት ቀናት ብቻ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ከታሪፍ በላይ ከማኅበረሰቡ የተወሰደ ገንዘብ ማስመለስ ተችሏል ነው ያሉት። ከሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል። ማኅበረሰቡ መብቱን እንዲያስከብር ሕዝብ የሚሠበሠብባቸው ቦታዎች ላይ የማወያየት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ለመብቱ ሲል ጥቆማ በመስጠት እየተባበረ ነው ብለዋል።

በዚህም የነዳጅ ግብይት ላይ ከጥቁር ገበያ ወደ መደበኛ ገበያ ሥርዓት የመመለስ ኹኔታ እንደታየ ነው የጠቀሱት። የሚሰቃየው ሕዝብ ነው ያሉት አዛዡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ማኅበረሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ዋና መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር በቀለ አብየ ማዕከላዊ ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ያለአግባብ የሚከፈል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ክፍያን የማስመለስ ተግባር እየተከናወነ መኾኑን ነግረውናል።

በተለይም የትራንስፖርት ፍሰት በሚበዛባቸው የክልሉ ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞች ላይ በስፋት እየተሠራ ነው ብለዋል። እንደ ፖሊስ አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ሕገወጥነቶችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አንስተዋል።

ያለ አግባብ የተከፈለ ገንዘብ ከማስመለስ ባለፈ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ የተገኙ ተሽከርካሪዎችን ተጠያቂ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል። ለአብነትም የክልሉ ዋና ከተማ በኾነችው ባሕርዳር ብቻ 80 የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች ተይዘው ባለቤቶች ተጠያቂ መኾናቸውን ገልጸዋል። ይህም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ማኅበረሰቡ ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ በትራንስፖርት ዘርፉ የሚፈጸሙ የተለያዩ የሕግ ጥሰቶችን ለማስተካከል የሚሠሩ ሥራዎች ላይ እየተባበረ እንደኾነም ገልጸዋል።

በቀጣይም የጸጥታ መዋቅሩን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን የተፈጠረውን ወቅታዊ የማኅበረሰብ ችግር ለመቆጣጠር መተጋገዝ እና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

#ትራንስፖርት_ታሪፍ #Ethiopia 🇪🇹

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous article“ከፍተኛ ባለሥልጣናትና አርቲስቶች ከ98 ቢሊየን ብር በላይ ዘርፈዋል” በሚል የተሠራጨው መረጃ የተሳሳተ ነው።
Next articleየምሥራቅ ዕዝ ኮር ከዱርቤቴ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደ።