
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሪፖርተር ጋዜጣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ.ም የዘጠኝ ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና የፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ሪፖርቱን ለማስረዳት በማስታወሻነት የተጠቀመበትን ጥቅል መረጃ መነሻ በማድረግ፣ ጠቅላላ ይዘቱን በአግባቡ ሳይረዳ እና በተቋሙ ስትራቴጂክ መሪዎች የቀረበውን ዝርዝር ማብራሪያ መጠቀም እየቻለ እውነታውን ወደ ጎን በመተው ሕዝብን በሚያሳስት መልኩ የተዛባ መረጃ በጋዜጣው የፊት ገፅ ላይ ይዞ ወጥቷል ሲል የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።
ሪፖርተር ጋዜጣ ከአንድ ቁንፅል ሀሳብ በመነሳት በማይገባ የሒሳብ ስሌት ውስጥ በመግባት 133 ሚሊየን 903 ሺህ 384 ዶላር ወደ ብር በመቀየር እና ከ78 ቢሊየን ብር ጋር በመደመር ከፍተኛ ባለስልጣናትና ታዋቂ አርቲስቶች ከ98 ቢሊየን ብር በላይ ዘርፈዋል በማለት ያሰራጨው ዘገባ ፍፁም የተሳሳተ ነው ብሏል።
እውነታው ግን 78 ቢሊየን ብር በየወንጀሉ ዓይነት ሲተነተን፦ 7 ቢሊየን ብር በሙስና ወንጀሎች (ከመዳበሪያ ግዥ እና ከባንክ ማጭበርበር ጋር የተያያዘውን ጨምሮ)፣ 6.4 ቢሊየን ብር በጉምሩክና ታክስ ወንጀሎች (ታክስ ስወራንና የኮንትሮባንድ ወንጀሎችን ጨምሮ)፣ 13.7 ቢሊየን ብር በተደራጁና ልዩ ልዩ ወንጀሎች (ሕገ-ወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እንዲኹም የማዕድን ዝውውርን ጨምሮ)፣ 44.9 ቢሊየን ብር በፋይናንስ እና ንግድ ነክ ወንጀሎች (ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ሀገር ዜጎች የተሳተፉበት ሕገ-ወጥ ሐዋላ፣ የሳይበር ወንጀል፣ የንግድ ነክ ወንጀል በተለይም ከፊንቴክ ድርጅት እና ከአርቲስቶች ጋር በተያያዘ በ1,400 ሰዎች ላይ የደረሰውን 1.7 ቢሊየን ብር ጉዳትን ጨምሮ) ነው።
እንዲሁም 6 ቢሊየን ብር የሚገመት በሽብርና በሌሎች የተለያዩ ወንጀሎች ላይ ጉዳት ከመድረሱ በፊት ማዳን የተቻለ እና አልፎም በደረሰ ጉዳት ላይም ምርመራ ማጣራቱን በዝርዝር ሪፖርቱ ተመላክቷል።
በተመሳሳይ ለተከበረው ቋሚ ኮሚቴ በቀረበው ሪፖርት ላይ 133 ሚሊየን 903 ሺህ 384 ዶላር ላይ ምርመራ ተጣርቶ ጉዳቱን ማዳን መቻሉ በዝርዝር ተገልጾ እያለ፤ ሪፖርተር ጋዜጣ ግን እንደተዘረፈ አድርጎ ለሕዝብ ያሰራጨው ዘገባ ከእውነታው የራቀና የተዛባ መኾኑ ተጠቅሷል።
ከላይ ከተዘረዘሩት ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በ9 ወር ውስጥ የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ 1,518 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ ተጣርቶባቸውና ክስ ተመስረቶባቸው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ኾነው እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡
እነዚህ ከላይ በዝርዝር የተጠቀሱት ወንጀሎችን በተመለከተ ፖሊስ በየጊዜው የደረሰበትን የምርመራ ውጤት ለሕዝብ ሲያሳውቅ እንደነበር ይታወቃል፡፡
እውነታው ይሄ ኾኖ ሳለ የሪፖርተር ጋዜጣ መረጃውን በትክክል ለሕዝብ ማድረስ ሲገባው አዲስ ነገር እንደተፈጠረ እና ኀብረተሰቡ እንደ ተዘረፈ አድርጎ ከጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ያፈነገጠና የጋዜጣው ስውር ተልዕኮ የተንፀባረቀበት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ፈፅሟል ብሏል በመረጃው።
በመኾኑም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሐሰተኛና የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር የፈጸመውን ሪፖርተር ጋዜጣን በሕግ አግባብ የሚጠይቅ መኾኑን አስታውቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
