
ባሕርዳር፡ ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አርበኞች በባዶ እግራቸው እየተመላለሱ ጠበቁሽ፤ እየራባቸው ቆሙልሽ፤ እየወደቁ አጸኑሽ፤ እየተገፉ አበረቱሽ፤ ከፊት እየቀደሙ ተጋረዱልሽ። የጠላትን ጦር በደረታቸው እያበረዱ ከጠላት መቅሰፍት ጠበቁሽ፤ ነጻነትሽን አጸኑልሽ፤ ጠላቶችን አሳፋሩልሽ፤ በከፍታ አስቀመጡሽ።
የመርዝ ጋዝ እየተደፋባቸው፤ የቦንብ ዝናብ እየዘነበባቸው፤ የጥይት አረር እንደ በረዶ እየወረደባቸው፣ ዓለም ፍትሕ ነፍጓቸው፤ የሀሰተኞች ፍርድ ቤት ዕውነታቸውን ጥሎባቸው ስለ ነጻነትሽ ጸኑልሽ፤ ስለ ክብርሽ በረቱልሽ። ብርታታቸው፤ ጽናታቸው እና ጀግንነታቸው ከተደፋባቸው የመርዝ ጋዝ ይበልጣል፤ ከዘነበባቸው የቦንብ ዝናብ ይልቃል።
አንቺ በአርበኝነት የቆምሽ፤ በጀግንነት የተጠበቅሽ፤ በጽናት የጸናሽ፤ በአንድነት የበረታሽ የነጻነት ምልክት፤ የጀግንነት አብነት ነሽ። አንቺ ልጆችሽ ለክብርሽ የሚሞቱልሽ፤ ለፍቅርሽ የሚደሙልሽ፤ ከአንቺ በፊት የሚቀድሙልሽ፣ ለሠንደቅ ዓላማሽ መከራን የሚቀበሉልሽ ጀግና ወላድ ነሽ። አርበኞች ነጻነትሽን ጠበቁልሽ፤ በጠላቶችሽ ፊት ግርማን ሰጡሽ።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 በተሰኘው መጽሐፋቸው ፋሽሽቱ የጣሊያን ወራሪ በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ተረጋግቶ መኖር አልተቻለውም። ኢትዮጵያ በታደለችው የተፈጥሮ ምሽጎች እየተጠቀሙ ደፈጣ ተዋጊዎቹ ጣሊያኖችን ጤና እና ፋታ ነሷቸው። በጀግንነታቸው እና በጦር ብልሃታቸው የኢትዮጵያን ነጻነት አስከብረዋል ብለው ጽፈዋል።
እነዚያ ጀግኖች ድል የነሱት ዝም ብለው አልነበረም፤ እየራባቸው፤ እየጠማቸው፤ እሾህ እና አሜካላው እየወጋቸው፤ የመርዝ ጋዝ እየተርከፈከፈባቸው ነበር እንጂ። እነርሱ ሞተው ለመጭው ትውልድ ነጻነትን አወረሱ። የሀገር ክብር እና ማዕረግ አለበሱ።
ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው በኢትዮጵያ የተካሄደውን የሚመስል የአርበኝነት ሥራ ከዚያ ቀደም በሌለ ሀገር ተካሂዶ አያውቅም ይላሉ። ንጉሠ ነገሥት አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ ውጭ ሲሄዱ የጦርነት ባሕል የሚያውቁትን ኢትዮጵያውያንን ተራራ እና ጫካን ተገን አድርገው እየተከላከሉ እንዲቆዩ አደራ ሰጥተው ነበር። ጀግኖች አርበኞችም አደራቸውን ተወጡ።
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች አዲስ የጦር መላ ፈጥረው፣ አዲስ የጦር ስልት ቀይሰው፤ ሀገራቸውን ከጥፋት፤ ወገኖቻቸውን ከእልቂት እና ከባርነት ለማዳን ተነሱ።
የአርበኞች ዓላማ አንድ ነበር፤ ኢትዮጵያን ነጻ ማወጣት፤ በዚህ ጉዳይ የወላወለ ከአርበኛ አይቆጠርም። ጀግኖች አርበኞች ደግሞ በሀገራቸው ነጻነት በፍጹም አይደራደሩም ነበር ይላሉ።
ጀግኖች አርበኞች ለሀገራቸው ቃል ገብተው፤ ለሠንደቅ ዓላማቸው ቃል ሰጥተው የጣሊያን ወራሪ እስትንፋስ እስክትቋረጥ ድረስ በጀግንነት ተዋጉ። በጀግንነትም ድል አደረጉ።
በአርበኞች ጀግንነት፣ ጽናት እና አንድነት የተበሳጨው የጣሊያን ፋሽሽስት በኢትዮጵያውያን ላይ አያሌ መከራ አደረሰ። ኢትዮጵያውያን ግን መከራ እያጸናቸው፤ ለበለጠ ድል እያስነሳቸው በጀግንነት ተፋለሙት፤ ጠላትንም ድል ነሱት።
“ጠላት ከሚጠጣው የሀገሬን ውኃ
የእኔ ደም ይቀዳ በዱር በበረሃ” እያሉ አርበኞች እንኳን ነጻነትሽን ውኃሽን ጠላት አይጠጣውም በማለት ተዋደቁ። ለሀገራቸው ነጻነት ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ። ክብሯን እና ሞገሷን አስጠበቁ። ወራሪውን ኃይልም በፊት እና በኋላ፣ በቀኝ እና በግራ ወጥረው አስጨነቁ። ከሀገራቸውም ምድርም ጠራርገው ጣሉት።
“ጠላትሽ ተዋርዶ ስምሽ እስኪከበር
እንሸከማለን የመከራን ቀንበር
እንግዲህ ባገሬ ነጭ ጤፍ አይብቀል
አረም ነው እያሉ ከሥሩ ነው መንቀል” እያሉ በጀግንነት ተዋጉ፤ ወደ ሀገራቸው የመጣውን የነጭ ወራሪ ድል መቱ። ለኢትዮጵያውያንም ነጻነትን፤ ክብርን እና ሞገስን ሰጡ።
የኢትዮጵያ ነጻነት የጸናው፤ የኢትዮጵያ ክብር የተከበረው በደም እና በአጥንት ነው። በአርበኞች ደም እና አጥንት። ጀግኖች አርበኞች ነጻነትን ስለሰጣችሁን፤ ክብራችንን ስላስጠበቃችሁልን እናመሠግናችኋለን፤ ታሪካችሁንም እንዘክራለን።
በታርቆ ክንዴ
#የአርበኞች_ቀን #Ethiopia 🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
