
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 (አሚኮ) የአርበኞች ቀን ቀደምት ኢትዮጵያውያን ወራሪን በመመከት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የከፈሉትን ታላቅ መስዋዕትነት በማሰብ ለ85ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ባለቤት እና መሥራች ኡስታዝ ጀማል በሽር የቀደምት ኢትዮጵያዊያን አርበኝነት ቀጥታ ቅኝ ገዥዎችን በአካል በመዋጋት እና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የሚገለጽ መኾኑን ገልጸዋል።
ቀደምት አባቶቻችን ድንበር ተሻግረው ኢትዮጵያን ለመውረር እና ቅኝ ለመግዛት የመጡ ወራሪዎችን አሳፍረው መልሰዋል ብለዋል። በዚህም ኢትዮጵያ “መቼም ያልተገዛች ሀገር” ኾናለች ነው ያሉት። አርበኛ አባቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት በአፍሪካ እና በአጠቃላይ ከጥቁሮች አገዛዝ እና ባርነት ጋር በተያያዘ የነጻነት አርማ፣ ምሳሌ እና ማሳያ ኾና እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ የምትጠቀስ ሀገር አስረክበውናል ነው ያሉት።
የማሸነፋቸው ምስጢርም አንድነት ነው ብለዋል። የውስጥ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ መቆማቸው እንደኾነ ገልጸዋል።
በዚህ ዘመን የኢትዮጵያን መበልጸግ የማይፈልጉ ጥንተ ጠላቶች በአካል አልሳካላቸው ሲል ሌሎች ስልቶችን እየሞከሩ እንደሚገኙ አንስተዋል።
አሳሪ ሕጎችን በማውጣት፤ በውኃ እና በድንበር ከኢትዮጵያ ጋር ከሚጋሩ ሀገራት ጋር በመተባበር፤ የባሕር በር አልባ እንድትኾን በማድረግ፤ በሀገር ውስጥ ‘ነጻ አውጭ ነን’ የሚሉ አካላትን በማደራጀት ኢትዮጵያን እረፍት በመንሳት ሀብቷን አልምታ እንዳትጠቀም ሲሠሩ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል። አሁንም እየሠሩ ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ጠንካራ አርበኝነት ይጠበቅበታል ብለዋል። ዘመኑ የሚጠይቀውን አካሄድ በመከተል የሀገሩን ክብር እና ጥቅም በማስከበር የአባቶቹን አርበኝነት ማስቀጠል እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
በልማቱ፣ በሰላሙ፣ በዲፕሎማሲው እና በሁሉም ዘርፍ የሀገሩ አምባሳደር ኾኖ ለሀገሩ ጥቅም መሥራት አለበት ነው ያሉት።
ትውልዱ የውኃ ሀብት፣ የሀገር ዳር ድንበር፣ የባሕር በር እና መሰል የጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመኾን መሥራት አለበት ብለዋል። ሀብቱን በማስከበር እና ጥቅም ላይ በማዋል ዳግማዊ አርበኝነትን መድገም ይገባል ነው ያሉት።
“በተለይ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ አርበኝነትን ሊኾን ይገባል” ነው ያሉት።
የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ፈለግ መከተል ይገበዋል ብለዋል። የግል ጥቅምን፣ የፖለቲካ ልዩነትን እና ቅሬታዎችን በሰላማዊ አግባብ በመፍታት ኢትዮጵያን ከነክብሯ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
#የአርበኞች_ቀን#Ethiopia 
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
