ሚሊሻ ለክልሉ መረጋጋት እና ሰላም የጀርባ አጥንት ኾኖ አገልግሏል።

23
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 27/2018 (አሚኮ) የሚሊሻ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ በተለያዩ ወታደራዊ ትርዒቶች እና ዝግጅቶችን ተከብሯል። በበዓሉ ላይ የአማራ ክልል ከፍተኛ መሪዎች፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች፣ የሚሊሻ ኮሚሽን መሪዎች እና የከተማ አሥተዳደሩ መሪዎች ተገኝተዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በዓሉ በአርበኞች ቀን መከበሩ የትናንትናውን ታሪካዊ ተጋድሎ ከዛሬው የሰላም ጥረት ጋር የሚያስተሳስር መኾኑን ገልጸዋል። ሚሊሻ ለክልሉ መረጋጋት የጀርባ አጥንት መኾኑንም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ሚሊሻ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለው አላምሬ ሚሊሻ በአንድ እጁ ማረሻ በሌላኛው እጁ ጠመንጃ ይዞ ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ኀይል መኾኑን ጠቅሰው መዋቅሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚታወቅ የሰላም አስከባሪ ኀይል መኾኑን አስገንዝበዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የሚሊሻ ሠራዊት በሀገር ፍቅር ስሜት እና በፈቃደኝነት ሕዝብን የሚያገለግል፣ ለከተማዋ ሰላም ዋስትና የኾነ የሰላም ዘብ መኾኑን ገልጸው ክብር እንደሚገባው ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከማል ኤጲሶ የሚሊሻን ታሪካዊ ተሳትፎ ሲያብራሩ “ያለ ሚሊሻ የካራማራን ድል ማሰብ አይቻልም” ብለዋል። አሁንም ለሠራዊቱ ዋነኛ አጋር እና የከተሞች የሰላም ዘብ በመኾን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልጸው መከላከያ የሚሊሻን አቅም ለመገንባት ዝግጁ መኾኑን አረጋግጠዋል።
በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የማርች ቡድን ወታደራዊ ትርዒት በማቅረብ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleአባቶች ለነጻነት ወደቁ፤ እኛ ለታላቅነት እንቆማለን።
Next articleየአሁኑ ትውልድ ለኢትዮጵያ ጥቅም ጠንካራ አርበኝነት ይጠበቅበታል።