
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የአርበኞችን የድል በዓል ምክንያት በማድረግ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም ሚያዝያ 27 ለእኛ የታሪክ ማኅደር ተገልጦ የሚነበብበት የትላንት ትዝታ ብቻ አይደለም፤ የአርበኞች አባቶቻችንን እና እናቶቻችንን የድል መንፈስ እንደ ብዕር በመጠቀም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ የጀመርንበት የትንሣኤ ጉዟችን መነሻ መሠረት ነው ብሏል።
ሚያዝያ 27 የነፃነት ማስታወሻ ብቻ ሳይኾን፣ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን በክብር ለመረከብ ላቡን የሚያፈስበት እና ያለውን የሚሰጥበት የቁርጠኝነት ቀን ነው።
ከ85 ዓመታት በፊት አባቶቻችን በደም እና በአጥንታቸው ሀገርን ጠብቀው የማቆየት ታሪካዊ ግዴታቸውን በድል ተወጥተዋል። ዛሬ የታሪኩ ምዕራፍ ተቀይሮ ተራው የእኛ ኾኗል፤ እነርሱ በነፃነት ያቆዩልንን ሀገር እኛ በዕውቀታችን፣ በላባችን እና በሥራችን የመገንባት የዘመኑ አርበኝነት አደራ አለብን ነው ያለው።
አባቶች በጠመንጃ ሀገር ጠበቁ፤ እኛ በቴክኖሎጂ ሀገር እንገነባለን። አባቶች ዳር ድንበር አስከበሩ፤ እኛ ድህነትን አሸንፈን ብልጽግናን እናረጋግጣለን። አባቶች ለነጻነት ወደቁ፤ እኛ ለታላቅነት እንቆማለን። ይህ የትውልድ ቅብብል ነው ብሏል።
ያለ አባቶች ጥበቃ ዛሬ የምንገነባት ሀገር ባልኖረች ነበር፤ ያለ እኛ ግንባታም አባቶች የጠበቋት ሀገር ትርጉም ያለው ሕይወት ለዜጎቿ መስጠት አትችልም። ትናንት በጀግንነት የተረከብናትን ሀገር፣ ዛሬ በሥልጣኔ አንጸን ለቀጣዩ ትውልድ የማስረከብ የሞራል ዕዳ፣ የሀገር አደራ አለብን።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያዊያን ከስንዴ ልመና ለመላቀቅ ወገባችንን አጥብቀን፣ ማረሻችንን ጨብጠን የተነሳነው፣ ለዚህ ነው ዓለም እኪደመም ተደምረን 48 ቢሊዮን ችግኝ የተከለነው፣ ለዚህ ነው ከመቀነታችን ፈትተን፣ ከጉርሳችን ቀንሰን ሕዳሴያችንን እውን ያደረግነው፣ ለዚህ ነው የዘመናት የጉስቁልና ምልክት የነበሩ ያረጁ ከተሞቻችንን ለመለወጥ እያመመን የበረታነው፣ ለዚህ ነው የከረሙ ስብራቶቻችንን ለመጠገን እንመካከር ያለነው፣ ለዚህ ነው ዙሪያው ተቸንክሮብን እስከመቼ እንኖራለን ያልነው፣ ለዚህ ነው የታዳሽ ኀይል መሠረት ለመጣል እየተጋን ያለነው ፣ ለዚህ ነው የአፍሪካ ትልቁን የአቬሽን ማዕከል እየገነባን ያለነው አደራ ስላለብን፣ ሀገርን በላብ የማሻገር አደራ ብሏል።
በዚህ ታሪካዊ ቀን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ለሀገሩ ጡብ የሚደረድር የራሱ ዘመን አርበኛ መኾን እንደሚጠበቅበት ገልጿል። ዛሬ እኛ የምናከናውናቸው የልማት ሥራዎች፣ የምናሳየው ጽኑ አንድነትና ዳር የምናደርሳቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሀገርን ጠብቀው ላቆዩን አባቶች የምንሰጠው ትልቁ የክብር መግለጫና የታሪክ ምላሻችን ነው።
ክብር ሀገርን ጠብቀው ላቆዩን አባቶች! በትጋት ሀገርን ለሚገነቡ ልጆች! ኢትዮጵያ በላባችን ታላቅ ትኾናለች!
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
