“ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ለሰው ልጅ ነጻነት እና ፍትሕ ጠበቃነቱን አሳይቷል” ጎሹ እንዳላማው

6
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት” ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር” በሚል መሪ መልዕክት የዓደባባይ ላይ የምርጫ ቅስቀሳውን አባላቱ እና ደጋፊዎቹ በተገኙበት አካሂዷል።
በብልጽግና ፓርቲ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሞላ ሁሴን መልዕክት አስተላልፈዋል። ብልጽግና ፓርቲ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ አሸንፎ ለመውጣት ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
ፓርቲው በከተማዋ ያስመዘገባቸውን የልማት ስኬቶችም አብራርተዋል። የኮሪደር ልማት፣ የሳይክል መንገዶች ግንባታ፣ የጣና ሐይቅን ለሕዝብ ክፍት ማድረግ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀው አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ውጤቶች መኾናቸውን ጠቁመዋል።
የፓርቲው የምርጫ ምልክት የኾነው የስንዴ ነዶ የብሔራዊ አንድነት፣ የመደመር እና የምርታማነት ተምሳሌት መኾኑን በማብራራት ነዋሪው ለቀጣይ ሰላም እና ልማት ሲባል ፓርቲውን እንዲመርጥ ጥሪ አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ብልጽግና ፓርቲ ሀገራዊ አንድነትን እና የዜጎችን ክብር ለማረጋገጥ ግልጽ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።
ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት “ለሰው ልጅ ነጻነት እና ለፍትሕ የቆመ መኾኑን በተግባር ማሳየቱንም” ጠቅሰዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የታዩት የልማት እና የውበት ለውጦች የፓርቲው ስኬት ጉልህ ማሳያ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
ከተማዋን የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ የማድረግ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልጽግና ይሠራልም ብለዋል።
የሀገር ብልጽግና ሲታሰብ የተጀመሩ እና እየተፈጸሙ ያሉ የልማት ትሩፋቶችን መመልከት በቂ ነውም ብለዋል። አሁንም በጉባ ብስራቶች የተበሰሩት የኢትዮጵያን ከፍታ እና ነጻነት የሚያረጋግጡ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን የሚኾኑት ብልጽግና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ ኾኖ ሲወጣ በመኾኑ ብልጽግናን ምረጡ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ጀግንነት ከሁሉም በፊት ሀገርን ማስቀደም ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
Next articleየታሪክ አደራ በአሁኑ ትውልድ ትከሻ ላይ ነው!