
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ቢበዙም በጀግኖች ልጆቿ ደም ታፍራ እና ተከብራ የኖረች የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ናት። ሚያዝያ 27 የአርበኞች ቀን ሲታሰብ፣ የታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን የፅናት፣ የአንድነት እና የሀገር ፍቅር ትልቅ ትምህርት ቤት ነው።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳዳር ትምህርት ክፍል መምህር ተስፋው አበባው እንዳሉት የዛሬው ቀን የኢትዮጵያ ጀግኖች ወራሪን ድል የመቱበትና ነፃነትን ያወጁበት ቀን በመኾኑ ከፍ ብሎ ይታወሳል።
የአባቶች የጀግንነት ፅናት ታሪክ የማይረሳ፣ ትውልድ የሚወርሰው፣ የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ቅርስ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ወጣት አበራ ድረስ በበኩሉ አርበኝነት ለሀገር ክብር መቆም ነው፤ ይሄ ከራስ ይጀምራል፤ ለዓላማ ጸንቶ በመሥራት የአባቶችን ታሪክና ሀገርን በሚያኮሩ ሥራዎች መድገም መኾኑን ተናግሯል። የሀገር ፍቅርን መውረስ፣ ፅናትን መልመድ አርበኝነትን በልማት ማሳዬት ይገባል ነው ያለው።
ከአርበኞች ታሪክ ምን እንማራለን?
አርበኞቻችን የዘር፣ የሃይማኖት እና የቋንቋ ልዩነት ሳይኖራቸው ለጋራ ሀገራቸው በአንድነት ቆመዋል። ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ክብር መሆኑን በተግባር አሳይተዋል።
ለአምስት ዓመታት (ከ1928-1933 ዓ.ም) በዱር በገደል፣ ድንጋይ ተንተርሰውና ቅጠል ለብሰው ያሳዩት ተጋድሎ፤ ለማንኛውም ችግር እጅ አለመስጠትን ያስተምረናል።
ሚስትና ልጆቻቸው ተማርከው እንኳ “ከቤተሰቤ ሀገሬ ትቀድማለች” በማለት ለሉዓላዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት የታማኝነት ጥግ ነው።
የዛሬው ትውልድ አርበኝነትን በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በልማት፣ በሥራ ጥንካሬ እና ለዓላማ በመጽናት ሊደግመው እንደሚገባ የአርበኞች ተጋድሎ ያስገነዝባል።
ታሪክ የዛሬው ትውልድ ማንነት መስታወት ነው። ሚያዝያ 27 ንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ድል አድራጊ ሆነው ወደ አዲስ አበባ የተመለሱበት ቀን ከመሆኑ ባለፈ፣ እኛም ነፃነታችንን የመጠበቅና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የማጠናከር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብን ያስገነዝበናል።
”ታሪክ ይወረሳል፣ ይወደሳል፤ በልጆች ይነግሣል፣ ነገም ይደገማል!”
ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
