ወጣቱ የአባቶቹን የጀግንነት ሥነ-ልቦና ተላብሶ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል።

11
ደብረ ታቦር: ሚያዝያ 27/2018 (አሚኮ) ለ85ኛ ጊዜ የሚከበረው የኢትዮጵያ አርበኞች ቀን መታሰቢያ በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር እና በደቡብ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ አስተባባሪነት “ክብር ለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች፣ የዞን እና የከተማ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አንባቸው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት ፋሽስት ጣሊያን በዓድዋ ሽንፈት ከተከናነበ በኋላ ለ40 ዓመታት ተዘጋጅቶ በዘመናዊ ጦር ዳግም ወረራ ቢፈጽምም አባት አርበኞች በደም እና በአጥንታቸው ተዋድቀው የሰንደቅ ዓላማቸውን ክብር ከፍ አድርገው ነፃነታቸውን አስከብረዋል ብለዋል።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የቆመችው እነዚህ አርበኞች “ለባዕድ አንገዛም” በሚል ወኔ በከፈሉት መሥዋዕትነት መኾኑንም አብራርተዋል።
አቶ አንባቸው አክለውም የአሁኑ ትውልድ አርበኝነትን በልማት፣ በሰላም እና በዕውቀት ሊገልጽ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሀገርን በቅንነት ማገልገል፣ ሌብነት እና ሙስናን ማውገዝ እንዲሁም ዘረኝነትን እና ጦርነትን መጥላት የዘመኑ አርበኝነት መገለጫዎች መኾናቸውን አሳስበዋል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አለበል ደመላሽ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አርበኞች የከፈሉት መሥዋዕትነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት ፋና ወጊ መኾኑን ገልጸዋል።
ወጣቱ የአባቶቹን የጀግንነት ሥነ-ልቦና ተላብሶ ራሱን በልማት ላይ ማዋል እና ለሰላም ዘብ እንዲቆምም ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየታሪክ አደራ በአሁኑ ትውልድ ትከሻ ላይ ነው!
Next articleሕገ ወጥ ግብይትን በመከላከል ማኅበረሰቡን ከብዝበዛ መታደግ ይገባል።