
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ85ኛው የዐርበኞች የድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢትዮጵያ ለዘመናት ታፍራ እና ተከብራ የኖረች፣ ሊወርሯት የሞከሩትን ያንበረከከች፣ የድል ታሪክ ባለ ክብረ ወሰን ናት ብለዋል።
ይህም የ ነው ነጻነታቸውን በምንም የማይለውጡ፣ ለሀገራቸው ክብር ሕይወታቸውን የማይሰስቱ ጀግኖች ልጆች ስላሏት ነው።
ከዛሬ 85 ዓመት በፊት የጥንት ጀግኖች ዐርበኞቻችን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አምስት ዓመታት ሙሉ በዱር በገደሉ ተጋድለው፣ ደማቸውን አፍስሰው እና አጥንታቸውን ከስክሰው ሀገርን አጽንተው አቆይተውልናል። ዛሬ የምንተነፍሰው የነጻነት አየር የእነዚያ ታላላቅ ባለታሪኮች የጽናት ውጤት ነው ብለዋል።
ዐርበኞቻችን ታሪክ የሠሩት የውስጥ ባንዳንና የውጭ ባዳን ድል ነሥተው ነው። እኛም የአባቶቻችን ልጆች በመኾናችን አሁንም ያንን ድል እንደግመዋለን ነው ያሉት።
ዛሬ የዐርበኝነት ትርጉሙ ዘርፈ ብዙ ኾኗል፤ የዚህ ዘመን ዐርበኝነት በሥራ መትጋት እና በዕውቀት መመራት፣ የድህነትን ታሪክ ለመቀየር ቆርጦ መነሣት፣ የተሻለች የነገዋ ኢትዮጵያን በላባችን መገንባት ነው።
ትውልዱ የአባቶቹን እና የእናቶቹን ታሪክ ማድነቅ ብቻ ሳይኾን፣ የራሱን አዲስ ታሪክ መሥራት ይጠበቅበታል። አሁን በድህነት እና በኋላ ቀርነት ላይ ዘምተናል፤ በሥራ ዐርበኝነትም ድል እያደረግናቸው ነው።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በዲፕሎማሲ መስኮች ድልን እያስቀጠልን፣ በተደመረ ዐቅም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ የሚያወጣ የዘመኑ ዐርበኛ ልንኾን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ዐርበኞች ኾይ ስለ ሀገር አንድነት እና ነጻነት ስለከፈላችሁት ውድ ዋጋ ዘላለም እናመሰግናለን፤
ክብር ለጀግኖች ዐርበኞቻችን ነው ያሉት በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
