
አዲስ አበባ: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ እየተከበረ በሚገኘው 85ኛው የአርበኞች ድል ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወራሪ የፋሽስት ኃይሎች ዘመናዊ የጦር መሣሪያ ይዘው ቢመጡም አርበኛ አባቶች እና እናቶች በጽኑ የሀገር ፍቅር ድል አድርገዋቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ነጻነት ስላረጋገጡልንም ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት ከንቲባዋ። ታሪክን በወጉ የሚዘክረው የመደመር መንግሥት የዓድዋ ሙዚየምን ጨምሮ የተለያዩ መታሰቢያ ሐውልቶችን በማደስ ታሪክን ለትውልድ ጠብቆ እያስተላለፈ ይገኛል ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ የዳግማዊ ዓድዋ ድል መገለጫ የኾነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመገንባት፤ የምግብ ሉዓላዊነትን በስንዴ በማረጋገጥ፤ በአረንጓዴ አሻራ እና ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ታሪክ መዘከር ብቻ ሳይኾን የራሱን ታሪክ እየጻፈ እንደሚገኝም አንስተዋል።
የትናንቱ አርበኝነት ሀገርን ከወራሪ በመስዋዕትነት በማዳን የተገለጠ ነበር፤ “የአሁኑ ትውልድ አርበኝነት ደግሞ ድህነት እና መከፋፈልን በመታገል ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያለአግባብ ያጣችውን “የባሕር በር ማስመለስ ከዘመኑ አርበኞች ትሻለች” ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሒም መሐመድ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
