
ወራሪው ኃይል በዘመናዊ መሣሪያ ጥቃት ሲሰነዝር አርበኞቹ ግን በባዶ እግራቸው በቆራጥነት መክተዋል። ይህ የነጻነት ተጋድሎ ለሀገር ዳር ድንበር መከበር ብቻ ሳይኾን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ልዩ ክብር እና ሞገስ እንድታገኝ ያስቻለ የታሪክ ገጽ ነው።
ይህ ተጋድሎ የኢትዮጵያውያንን ማንነት ዳግም ገልጧል፣ አይበገሬነቷንም ለዓለም አሳይቷል። በዓለም አደባባይ ከፍ ያለ የክብር ማማ ላይ እንድትቀመጥም አስችሏታል። ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የጀግንነት ተምሳሌት ኾና በኩራት እንድትጠራ አድርጓል።
በጅንካ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ተስፋየ ገብረማርያም እንዳስረዱት የአርበኞች ተጋድሎ ለኢትዮጵያ ክብር ብቻ ሳይኾን በጭቆና ስር ለነበሩት ለመላው አፋሪካውያንም ትምህርት የሰጠ ነበር።
አርበኞቹ በጫካ፣ በዱር እና በገደሉ በከፈሉት ተጋድሎ ቅኝ ግዛትን አልቀበልም በማለት ላሳዩት ጽናት መላው የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን በከፍተኛ አድናቆት እንዲመለከቷት አድርጓል። አፍሪካውያን ለነፃነት ላደረጉት ትግል መነሻም ኾኗቸዋል ነው ያሉት።
ለፓን አፍሪካኒዝም መወለድ፣ ለአፍሪካ ኅብረት መመስረትም ቁልፍ ሚና እንድትጫወት መሰረት ጥሏል። በአውሮፓውያን ዐይን ሳይቀር ኢትዮጵያ የነፃነት እና የጀግንነት ተምሳሌት ኾና እንድትታይ ያደረገው ይኸው የአርበኞች እምቢተኝነት ነበር።
መምህሩ እንዳብራሩት የኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጋድሎ ዓለም አቀፋዊ ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ማሳየ ነው።
በዘመኑ ያሳዩት ይህ ጀግንነት እና ድል አድራጊነት ዓለም ለኢትዮጵያ ታላቅ እውቅና እንዲሰጥ አስገድዷል። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተሰሚነት እንዲኖራት ተጽዕኖው የጎላ ኾኗል።
አርበኞቻችን በደማቸው የጻፉት ታሪክ ኢትዮጵያን የነፃነት ፋና ወጊ አድርጓታል። ዛሬም ድረስ የሚነሳው የአርበኝነት የጀግንነት ታሪክ ለኢትዮጵያ የክብር መሠረት ኾኖ ዘልቋል። ለቀጣዩ ትውልድም ኩራትን እና ጽኑ የሀገር ፍቅርን የሚያስተምር ኾኖም ሲዘከር ይኖራል።
በአሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
