
ባሕዳር፡ ሚያዚያ 27/2018ዓ.ም (አሚኮ) የአርበኞች ቀን የድል ቀን ብቻ አይደለም። የቀደምት አባቶችን ተጋድሎ፣ የሀገር ፍቅር፣ ጽናት፣ አንድነት እና ኢትዮጵያዊ ሥነልቦና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተምር ትልቅ የታሪክ መዝገብ ጭምር ነው።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ገረመው እስከዚያ (ዶ.ር) ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ ልዩ ቦታ እንደነበራቸው እና አሁንም እንዳላቸው ነግረውናል። ታሪክ እንደሚያስረዳው ቀደምት አባቶች እና እናቶች በሀገራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በባንዲራቸው እና በክብራቸው ድርድር የላቸውም ነበር ነው ያሉት። የአርበኞች ቀን ሚያዚያ 27 ተከብሮ የሚውለውም ያንን ታሪክ ለማሰብ እና የዋሉትን ውለታ ለመዘከር መኾኑን ገልጸዋል።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ሲያዙ ኢትዮጵያ ግን ያንን መክታ ነጻነቷን ያስጠበቀች እና ደማቅ ታሪክ የጻፈች ሀገር እንደኾነችም አስታውሰዋል። ደማቅ የኢትዮጵያዊነት ታሪክ ከተጻፈበት የዓድዋ ድል እና የፋሽስት ኢጣሊ ዳግም ወረራ በፊት ጠላቶቿን በመመከት በርካታ ተጋድሎ ማድረጓንም ጠቅሰዋል። በአብነትም ግብጾችን፣ መሃዲስቶችን እና ጣሊኖቸን በውጊያ የመመከት ሂደት እንደነበራት አንስተዋል።
በርካታ የኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፍ ጸሐፊዎችም ታሪኩን በስፋት በመጻፍ ለዓለም በማስተዋወቃቸው ኢትዮጵያዊነትም በስፋት ታውቋል ብለዋል። ሀገር እና ሕዝብ ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን መንግሥት እና ንጉሠ ነገሥቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብለው እንዲታወቁ አድርጓል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊነት ማንነት ነው ያሉት ምሁሩ ይህ ማንነት በቀደምት አባቶች እና እናቶች ተከብሮ እንደቆየ ሁሉ አሁን ላይ ያለው ትውልድ ይህን መጠበቅ እና ማስከበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ሀገሪቱ በዘመናዊ መንገድ እንድትለማ፣ እንድታድግ እና ኢትዮጵያም የበለጠ ጠንካራ ሀገር እንድትኾን ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ መበርታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ሊያጠቃ የሚችልን ኀይል ወደፊትም መመከት እንደሚያስፈልግ ነው ያስገነዘቡት። “ጠንካራ ኹነን ከተገኘን ማንም አይደፍረንም” ፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትም ዘላለማዊ ኹነው ይቀጥላሉ” ብለዋል።
ውስጣዊ የእርስበርስ አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን ካለፉት ተመሳሳይ ታሪኮች ትምህርት በመውሰድ በጋራ መፍታት እንደሚገባ መክረዋል።
የውስጥ ችግር ከተፈታ የውጭ ጣልቃ ገብነት አይኖርም ነው ያሉት። ሰው እና ግጭት ምንጊዜም የማይለያዩ ቢኾኑም ችግሮች ችግር እንዳያመጡ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠይቃል ብለዋል። ችግሮችን መከላከል እና በሰላማዊ መንገድ በመፍታት የእያንዳንዱ ዜጋ እሳቤ እና ድርሻ መኾን እንደሚገባውም መክረዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
