ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የነጻነት ንቅናቄ አስኳል ናት።

6
🇪🇹ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ታጋይነት አንድ ግለሰብ ብቻውን ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለ ሀገር ክብር የሚያካሂደው ተጋድሎ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ደግሞ የታጋይነት ቁልፍ ማሳያ ናቸው።
አርበኞች በጦር እና በጎራዴ የጠላትን መሣሪያ እየቀሙ ስለ ሀገር ተዋድቀዋል። ለሹመት እና ለሽልማት ሳይኾን ለሀገር ነጻነት፤ ለወገን ደኅንነት መቆማቸውን አረጋግጠዋል።
እንደ አበበ አረጋይ፣ በላይ ዘለቀ፣ ሽዋረገድ ገድሌ ከመሳሰሉ ጀግና አርበኞች ባሻገር የሃይማኖት አባቶችም በክብር ስለ ሀገር ፍቅር በጀግንነት ዋጋ እንደከፈሉ ታሪክ ምስክር ነው።
ለዚህ ማሳያ ቆራጡ የሃይማኖት አባት አቡነ ጴጥሮስ ይጠቀሳሉ። የጣልያንን መንግሥት እንዲደግፉ ሲጠየቁ ሕዝቡም፣ ምድሪቱም ለጣልያን መንግሥት እንዳይገዙ ገዝተው በክብር ስለሀገራቸው ሕይወታቸውን የገበሩ ናቸው፡፡
ድል እንጅ ሽንፈት የማያውቁት የኢትዮጵያ አርበኞች የአፍሪካ ኩራት እና ተምሳሌት መኾን እንደቻሉ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ድፌንስ መከላከያ ኮሌጅ የታሪክ አሥተማሪ እና ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሬ ጣሊያን ዓድዋ ላይ የቀመሱትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት በኋላ ቅኝ ለመግዛት መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የጣሊያን ወረራ ወደ ፊት እየገፋ ሲመጣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በካቢኒዎቻቸው ውሳኔ መሠረት የውጭ ድጋፍን ለማግኘት፣ የኢትዮጵያን መብት ለማስከበር እና ለዓለም ለማሳወቅ ወደ እንግሊዝ መሄዳቸውንም ገልጸዋል።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ጣሊያን አዲስ አበባን መቆጣጠራቸውን አንስተዋል። በወቅቱ የመርዝ ጋዝ እና ሌሎች መሥሪያዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ነው የተናገሩት።
አርበኞች በጎበዝ አለቃ በመደራጀት ቀጥሎም በአንድነት በመሰለፍ መስዋዕትነት ከፍለዋል ነው ያሉት። በዚህም ድል ማድረግ እንደቻሉ ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ድልን በማስመዝገብ የጥቁር ሕዝቦችን መብት በማስከበር፣ ነጻነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት መኾን እንደቻለች ጠቅሰዋል። “ለአፍሪካውያን የነጻነት ንቅናቄ አስኳል” መኾኗንም ጠቁመዋል።
ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን በብሔር፣ በሃይማኖት እና በቋንቋ ለመካፋፈል መሥራታቸውን አንስተዋል። በሁሉም ቦታ ሕዝቡ በአንድነት ጠላትን ለማባረር መተባበሩንም ገልጸዋል።
የሀገር ፍቅር የሚገለጸው ሕይወትን እስከ መስዋዕትነት በማቅረብ ነው ብለዋል። ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን ማወቅ እና ከታሪኩ መማር አለበት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ዛሬም የአፍሪካ ተምሳሌትነቷን ለማስቀጠል የአፍሪካን ታሪክ የሚገልጽ ሙዚየም በመገንባት እና ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመኾን አፍሪካውያንን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሃሳብ በማቅረብ እየሠራች ነው ብለዋል።
የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፤ ሰላማዊ ግንኙነትን በማጠናከር፤ ሀብትን በጋራ እና በአግባቡ በመጠቀም ድህነትን በማሸነፍ ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም አፍሪካዊ ተምሳሌትነቷን ማስቀጠል አለባት ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous article“ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘከር ወደፊት ለመስፈንጠር ፋይዳው የጎላ ነው” አሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)
Next article“ኢትዮጵያዊነት ማንነት ነው፤ ይህን ማንነት ማስከበር ደግሞ የትውልዱ ድርሻ ነው”