“ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘከር ወደፊት ለመስፈንጠር ፋይዳው የጎላ ነው” አሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)

5
ደሴ፡ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሚሊሻ መምሪያ የክልሉ የሚሊሻ 30ኛ ዓመት በዓል እና የዕውቅና መርሐግብር አካሂዷል።
አሚኮ ያነጋገራቸው ሚሊሻዎች የተሰጠን ዕውቅና ለቀጣይ ሥራ የሚያነሳሳ እና ሀገር ውለታችንን እንዳልዘነጋችው ያሳየን ነው ብለዋል። በቀጣይም የክልሉ ሰላም ለመጠበቅ አስፈላጊውን መስዋትነት እንደሚከፍሉ ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ ሚሊሻ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ጌታወይ ዘገየ ዕለቱ ረጅሙን የሚሊሻ ጉዞ የምንዘክርበት ፊት ለፊታችን ደግሞ ኀላፊነት የምንረከብበት ነው ብለዋል።
በከተማው ያሉ ሚሊሻዎች የከተማዋን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን ከሀገር ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመኾን የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ ወታደራዊ ግዳጆችን እየተወጡ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ ዕውቅናው ሚሊሻዎች ሕገ መንግሥቱ እንዲጸና እና ሀገር ተከብራ እንድትኖር የሠሩትን የማይተካ ሚና ለመዘከር የታሰበ መኾኑን ገልጸዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ11ኛ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ዘውዱ ሰጥአርጌ የውትድርና ታሪካችንን ስንመረምር ከጣሊያን ወረራ ዘመን ጀምሮ ሚሊሻነት ታሪካችን ነው ብለዋል።
በዚያድባሬ የሶማሊያ ወረራ ወቅትም ሚሊሻው ታሪክ ሠርቷል ነው ያሉት። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ላይም ሚሊሻው አኩሪ ገድል መፈጸሙን አስታውሰዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ላይም ውድ ሕይወቱን ከፍሎ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ቆሞ ሀገሩን የታደገው ሚሊሻ መኾኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት ክልሉ ከገባበት ችግር ለመታደግ መሪዎችን በማገዝ እና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም እያደረገ ያለውን ጥረት ትውልድ ይዘክረዋል ብለዋል።
ክልሉ የሰጠው ዕውቅና የሚያስመሠግነው መኾኑንም ተናግረዋል። በቀጣይም ሚሊሻው ራሱን ለላቀ ግዳጅ እያዘጋጃ በሥነ ምግባር ታንጾ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኅላፊ አሸቱ የሱፍ (ዶ.ር) ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘከር ወደፊት ለመስፈንጠር ፋይዳው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል። የአማራ ክልል ሚሊሻ የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት በላቀ ሁኔታ እንዲያገለግል በተጠናከረ መልኩ እየተደራጀ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለሚሊሻ አባላት የሚገባቸው ጥቅማ ጥቅም ተከብሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።  በዓሉ የምሥጋና፣ የአንድነት ማጠናከሪያ፣ ተጋግዞ የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ ቃል የሚገባባበት እና በቀጣይም አስፈላጊው መስዋትነት ተከፍሎ ሰላም ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ስለመኾናችን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦አበሻ አንለይ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleበአማራ ክልል የተማሪዎች የዓይን ጤና ልየታ ሥራ ተጀመረ።