በአማራ ክልል የተማሪዎች የዓይን ጤና ልየታ ሥራ ተጀመረ።

3
ደብረ ብርሃን: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ዓይነ ሥውርነትን ለመከላከል እና የዕይታ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለመርዳት የሚያስችል የዓይን ጤና ልየታ ሥራ ተጀምሯል።
ይህ የልየታ ተግባር በባሕር ዳር፣ በጎንደር እና በደብረ ብርሃን ከተሞች በሚገኙ ሁሉም የቅድመ መደበኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከናወን ተገልጿል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ብሩህ ተስፋ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በተካሄደው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች ኦፊሰር እና የዓይን እና አዕምሮ ጤና ተጠሪ ዶክተር ፈቃደ አድማስ የዓይን ጤና ችግርን ቀድሞ በመለየት ዓይነ ሥውርነትን መከላከል ይቻላል ብለዋል።
ቀደም ሲል ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን አስታውሰዋል። አሁን ላይ የሕጻናትን የትምህርት ተሳትፎ እና ውጤታማነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
የፓርትነርስ ኢን ኢዱኬሽን ኢትዮጵያ የጤና ፕሮግራም አሥተባባሪ የማርናት አዱኛ የልየታ ሥራው ከተከናወነ በኋላ የዕይታ ችግር ላጋጠማቸው ተማሪዎች የነጻ ሕክምና እና የመነጽር ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ድጋፉ ከክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የሚከናወን ነው። በተለይም ዕድሜያቸው ከ1 እስከ 10 ዓመት የኾኑ ሕጻናትን ታሳቢ ያደርጋል ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ብቻ 14 ሺህ መደበኛ ተማሪዎች እና በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 3 ሺህ ሕጻናት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ መቅደስ ብዙነህ ልየታው ወላጆች የልጆቻቸውን የዕይታ ችግር ሳያውቁ የመቆየታቸውን አጋጣሚ እንደሚቀነስ ተናግረዋል። የመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ እንዲኾን የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ የግል እና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ የዓይን በሽታን ለመከላከል ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።
መምሪያው የባለሙያ ድጋፍን ጨምሮ አስፈላጊውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። የዓይን ጤና ልየታ እና ሕክምናው በደብረ ብርሃን ከተማ ለቀጣይ ሁለት ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ መንግሥት እና ባለሀብቶች ተቀራርበው መሥራት አለባቸው።
Next article“ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘከር ወደፊት ለመስፈንጠር ፋይዳው የጎላ ነው” አሸቱ የሱፍ (ዶ.ር)