የክልሉ ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ መንግሥት እና ባለሀብቶች ተቀራርበው መሥራት አለባቸው።

3
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ከፍተኛ መሪዎች በኢንቨስትመንት ከተሠማሩ ባለሀብቶች ጋር በባሕር ዳር ከተማ መክረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ ቀልጣፋ አሠራሮች እንዲተገበሩ፤ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ፤ የኃይል አቅርቦት ችግሮች እንዲቀረፉ እና የብድር አቅርቦት አማራጮች እንዲሰፉ ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ዘመናዊ ከተማ የመፍጠር ጉዟችንን መሠረት እየጣልን ነው ብለዋል። ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ከተማዋን የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግም 300 ሄክታር መሬት የኢንዱስትሪ መንደር ተለይቶ ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በከተማዋ የሚሰጡትን አገልግሎቶች የተሳለጡ ለማድረግ የድጅታላይዜሽን ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መኾናቸውን አንስተዋል። ባሕር ዳር ከተማ በአስተማማኝ ሰላም እና በፈጣን የልማት ጉዞ ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አሥተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት ከሕግ ማስከበሩ ጎን ለጎን በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናቅቆ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጸዋል።
ኢንቨስትመንቱን ለማነቃቃት በሚደረገው ጥረት ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ነው ያሉት።
መንግሥትም በአልሚ ባለሀብቶች በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን ወስዶ ደረጃ በደረጃ በመፍታት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleበአማራ ክልል የተማሪዎች የዓይን ጤና ልየታ ሥራ ተጀመረ።