
ደብረታቦር፡ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ መኽኑን ገልጿል።
ምርጫው በስኬት እንዲጠናቀቅ ከሰላም አስከባሪ፣ ከአድማ መከላከል፣ ከፍትሕ ተቋማት እና ከሕዝቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑንም አስታውቋል።
የፋርጣ ወረዳ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ዋና አዛዥ ኢንስፔክተር አበበ ባየ እንደገለጹት ኅብረተሰቡ የምርጫ ካርዱን ያለ ስጋት እንዲወስድ አስፈላጊው የጥበቃ ሥራ ሲከናወን ቆይቷል።
ለጸጥታ መዋቅሩ አስፈላጊው ሥልጠና ተሰጥቶ ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል። ሰላምን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ አካላት ከመንግሥት የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርበዋል። ኅብረተሰቡም የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ካሉ ጥቆማ በመስጠት ከፖሊስ ጋር እንዲተባበር አሳስበዋል።
የወረዳው ሰላም አስከባሪ አባል ቀለብ ጣሰው ዜጎች ካርዳቸውን እንዲወስዱ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ የምርጫን አስፈላጊነት ተረድቶ ድምጹን እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የወረዳው ነዋሪዎችም መብታቸውን ለመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ካርድ መውሰዳቸውን እና ድምጻቸውን ለመስጠት በጉጉት እየጠበቁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
