በክልሉ 67 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሠብሥቧል።

5
ደብረብርሃን፡ ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የሰሜን ሸዋ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ የደብረ ብርሃን እና የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደሮችን የሥራ አፈጻጸም በደብረ ብርሃን ከተማ ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እንዳሉት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 67 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ ተችሏል።
የተሠበሠበው ገቢ የዘጠኝ ወራት ዕቅዱን 67 በመቶ ያህሉን የሸፈነ ነው ብለዋል። ኀላፊው በክልሉ የሚከናወኑ ማናቸውም የልማት ሥራዎች ስኬታማ እንዲኾኑ የገቢ አሠባሠብ ሥራው በትኩረት መከናወን እንደሚገባውም አመላክተዋል።
የገቢ አሠባሠቡን ዘመናዊ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት በኤሌክትሮኒክስ የታክስ ሥርዓት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብሥቧልም ብለዋል።
በቀሪዎቹ የበጀት ዓመቱ ወራት ግብር ከፋዩ ግዴታውን እንዲወጣ እና ተባባሪ እንዲኾንም ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የሰሜን ሸዋ ዞን ገቢዎች መምሪያ የዘጠኝ ወራት ዕቅዱን 74 በመቶ በማሳካት ከሌሎች ዞኖች የተሻለ አፈጻጸም ማሳየቱ ተገልጿል።
የመምሪያው ኀላፊ ቀለም ተስፋዬ በቀሪ ወራት ዕቅዱን 100 በመቶ ለማድረስ የትኩረት አቅጣጫዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።
በሰሜን ሸዋ ዞን የግብር ከፋዮችን የግንዛቤ ደረጃ ማሳደግ በቀጣይ እንደ ዋነኛ የሥራ ተግባር ተይዟል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል የምሥራቅ ጎጃም ዞን በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሠብሠብ መቻሉ ታውቋል።
የዞኑ ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጥሩምርት አለልኝ የጸጥታ ችግሮች በገቢ አሠባሠቡ ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ገልጸዋል።
ከጸጥታው በተጨማሪ የግንዛቤ ክፍተት መኖር በምሥራቅ ጎጃም ዞን ለገቢው ዝቅተኛ መኾን በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ይሁን እንጂ የገቢ አሠባሠብ ሥራን “የህልውና ጉዳይ” በማድረግ በቀሪ ወራት ርብርብ እንደሚደረግ ወይዘሮ ጥሩምርት አረጋግጠዋል።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ መሰል የግምገማ መድረኮችን በየቀጣናው በማካሄድ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን እየለየ እንደሚገኝም በመድረኩ ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ለዓለም ለይኩን
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleየደሴ ከተማ አሥተዳደር ለ96 የቤት ማኅበራት የቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ።
Next articleሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል።