የደሴ ከተማ አሥተዳደር ለ96 የቤት ማኅበራት የቤት መሥሪያ ቦታ አስረከበ።

6
ደሴ: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር በጋራ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት ለተደራጁ ነዋሪዎች የሳይት ርክክብ እና ዕጣ የማውጣት መርሐ ግብር አከናውኗል።
አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡት በጋራ መኖሪያ ቤት ማኅበር ተደራጅተው ሲጠባበቁ የነበሩ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ ለዓመታት ሲያቀርቡት የነበረው የቤት መሥሪያ ቦታ ጥያቄ ምላሽ በማግኘቱ ደስ ብሎናል ብለዋል።
በቤት ኪራይ እና በኑሮ ውድነት ተማረው መቆየታቸውን ገልጸዋል። በተቀመጠው መስፈርት መሠረት ቤታቸውን በፍጥነት ለመገንባት ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከተማ አሥተዳደሩ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ነዋሪዎችን በማደራጀት የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
ዛሬ በጋራ የመኖሪያ ቤት ማኅበራት ለታቀፉ ለ6 ሺህ 400 በላይ ነዋሪዎች የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
በከተማዋ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በማኅበር የተደራጁ የቤት ፈላጊዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ላቀረቡት ጥያቄ ከተማ አሥተዳደሩ 117 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ለአንድ ማኅበር 1 ሺህ 500 ካሬ ቦታ ማስረከቡንም ጠቅሰዋል።
በመርሐ ግብሩ ባለ 1መኝታ አራት ማኅበር፣ ባለ 2 መኝታ 56 ማኅበር፣ ለባለ 3 መኝታ 36 ማኅበር ተጠቃሚ ይኾናሉ ነው ያሉት።
ግንባታ ከመጀመሩ በፊት አስፈላጊ የኾኑት መሠረተ ልማቶችን ቀድሞ የማሟላት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን ለማሟላት ይሠራልም ተብሏል።
በመርሐ ግብሩ ለጋራ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበር ለተደራጁ 96 ማኅበራት ሳይትፕላን ርክክብም ተካሂዷል።
ዘጋቢ:-መስዑድ ጀማል
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
Previous articleባለሃብቶች ወደ ክልሉ ገብተው እንዲያለሙ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ጥሪ አቀረቡ።
Next articleበክልሉ 67 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሠብሥቧል።