
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በኢንቨስትመንት የተሠማሩ ባለሃብቶችን በባሕር ዳር ከተማ አወያይተዋል።
ክልሉ ትልቅ ጸጋ ያለው፣ ታታሪ እና ሥራ ወዳድ ሕዝብም ያለበት ክልል መኾኑን ገልጸዋል። በአየር ንብረት እና በተፈጥሮ ጸጋ ለኢንቨስትመንት ሰፊ አቅም ያለው ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ለውጭ ገበያ እና ለሀገር ውስጥ ፋብሪካዎች ግብዓት የሚኾን የሰብል ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት ትልቅ አቅም እንዳለም ጠቁመዋል።
በአትክልት እና ፍራፍሬ፤ በእንስሳት ሃብት ልማትም ትልቅ አቅም ያለው እንደኾነ ገልጸዋል። ሰፊ የማዕድናት ክምችት እንዳለም ጠቁመዋል። ለአብነትም የብረት፣ የኦፓል እና የወርቅ ማዕድናት ክምችቶች በስፋት እንደሚገኙ አንስተዋል።
ግዙፍ ፋብሪካዎችን ለማስፋፋት የሚያስችል መሠረተ ልማት እና ለግንባታ ግብዓት የሚኾኑት የሲሚንቶ፣ግራናይት እና ማርብል ሃብቶችም አሉ ነው ያሉት።
ታሪክን፣ ባሕልን፣ ቅርስን እንዲሁም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን መሠረት ያደረገ ያልተነካ የቱሪዝም ጸጋ ስለመኖሩም አንስተዋል።
መንግሥት የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማቶችን እያሟላ መኾኑን የጠቆሙት ርእሰ መሥተዳድሩ በአሁኑ ወቅት ተስፋ የሚሰጥ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ መኖሩን አመላክተዋል።
ማንኛውም ባለሃብት በየትኛውም የክልሉ አካባቢዎች እንዲያለማ የሚያበረታቱ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በተለይም በከተሞች በየዓመቱ በርካታ ፋብሪካዎች እየተገነቡ ወደ ሥራ እየገቡ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ባለሃብቶች ወደ ክልሉ በመግባት እንዲያለሙ ርእሰ መሥተዳድሩ ጥሪም አቅርበዋል። ባለሃብቶችን አላሠራ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት ቁርጠኛ ኾኖ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
