
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚሠራውን የፎር ፖይንት ባይ ሸራተን ባሕር ዳር ጣና ሆቴል ፕሮጄክትን አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ “በውቢቷ ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ሆቴል ሊገነባ በመኾኑ ደስታ ተሰምቶኛል” ብለዋል። ሜድሮክ ኢንቨስትመንት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያመጣው ለውጥ የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል ።
በጎደለ ጊዜ የሚገኝ ትልቅ ድርጅት መኾኑን ነው የገለጹት። ሜድሮክ ችግሮችን ተቋቁሞ ከዚህ የደረሰ ብርቱ ድርጅት መኾኑንም ገልጸዋል።
ድርጅቱ በርካታ ሠራተኞችን አቅፎ የያዘ መኾኑንም አንስተዋል። ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በታላላቅ ፕሮጄክት ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ መኾኑን ነው የተናገሩት። በችግር ጊዜ ቀድሞ የሚገኝ፤ የሀገርን ልማት የሚደግፍ መኾኑን ነው ያነሱት።
የተጀመረው ፕሮጄክት በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ለባሕር ዳር ትልቅ ጸጋ ነው፤ ጎብኝዎችን፤ የሀገር መሪዎችን ለማምጣት እና የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። በቅንጅት እና በቁርጠኝነት ከሠራን በአጭር ጊዜ ውስጥ እናጠናቅቀዋለን ነው ያሉት።
ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሌሎች ልማቶች ያሳየውን ብቃት በሆቴል ፕሮጄክት ላይም መድገም እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
