
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚሠራውን የፎር ፖይንት ባይ ሸራተን ባሕር ዳር ጣና ሆቴል ፕሮጄክትን አስጀምረዋል።
በማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና ሌሎችም ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የዚያስ ዲዛይን ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አሥኪያጅ ደረጀ አሰፋ የጣና ሆቴል ከ49 ዓመታት በፊት እንደተገነባ ገልጸዋል። በየጊዜው ዕድሳት ሲደረግለት እንደቆየም ተናግረዋል። አሁን ግን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ይሠራለታል ነው ያሉት።
የፎር ፖይንት ባይ ሸራተን ባሕር ዳር ጣና ሆቴል ለባሕር ዳር መጣላት፤ ዕድለኛ ናት የሚሉ አሉ ያሉት ሥራ አሥኪያጁ የባሕር ዳርን ውበት ያዩ ግን ዕድለኛው ገንቢው ነው ብለዋል።
ፕሮጄክቱ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል። 120 ዘመናዊ አልጋዎች ያሉት ሆቴሉ ቅንጡ እና ዘመናዊ ኾኖ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የጣናን ሌላኛውን መልክ የሚያሳይ፤ ተጨማሪ ውበት እና የቱሪዝም ሃብት ነው ብለዋል።
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩም ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጀመል አሕመድ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በውቢቷ ባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል እንደሚሠራ ገልጸዋል። ሆቴሉ መንግሥት ለጀመረው የቱሪዝም እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ፕሮጄክቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ እንደሚሠራም አንስተዋል። ሆቴሉ በ18 ወራት ይጠናቀቃል ነው ያሉት።
ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለሀገር ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል። ሆቴሉ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
