“ሀገር እና ሕዝብን የሚያስከብሩ፣ ለትውልድም የሚተርፉ ሥራዎች እየሠራን እንገኛለን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

5
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ የተገነባውን የፈለገ ግዮን ኢኮ ሪዞርት መመረቅ አስመልክተው በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልእክት አስተላልፈዋል። የመልእክታቸው ሙሉ ይዘትም እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በዓይነቱ ልዩ የሆነውን የፈለገ ጊዮን ሪዞርትን መርቀን ሥራ አስጀምረናል። ፈለገ ጊዮን ለባሕርዳር ከተማ ተጨማሪ ጸጋን የገለጠ ሪዞርት ነው።
አማራ ክልል የአኩሪ ታሪክ ባለቤት፤ በተፈጥሮ የታደለ፣ በባሕልና እሴት የዳበረ፣ አስፈላጊ የቱሪዝም መዳረሻ ሃብት ያለው ክልል ነው።
በአንድ ዓለት ላይ የጸኑ አብያተክርስቲያናት፣ በሐይቅ ላይ የታነጹ ገዳማት፤ በጡብ የተዋቡ አብያተ መንግሥታት፤ የጥንት ታሪክ የሚነገርባቸው መስጊዶች፣ ብርቅዬ እንስሳት የሚገኙባቸው በተፈጥሮ የተዋቡ ተራራዎች አሉት።
ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ በትውልድ ቅብብሎሽ የመጡ ባሕል እና ወጎች፣ ዘመናትን የተሻገሩ ታሪኮች፣ የጥንት ታሪክ የሚገለጥባቸው፤ ዕውቀት እና ጥበብ የሚመረመርባቸው የሥነ ጽሑፍ እና የኪነ ጥበብ ውጤቶች ያሉበትም ነው።
“በሞቴ አፈር ስኾን እያለ” እንግዳ የሚቀበል ደግ ሕዝብ የሚኖርበት ጎብኝዎች አብዝተው የሚወዱት ክልልም ነው። መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት አማራ ክልል ከጥንት ከነበሩት ታሪካዊ ሥፍራዎች፣ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች፣ ተፈጥሯዊ መዳረሻዎች እና ጸጋዎች ባሸገር ለክልላችን ተጨማሪ ውበት እና በረከት የሚሆኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየገነባን ነው።
ከዓመት በፊት በጎርጎራ፣ ከሁለት ከሳምንታት በፊት በሎጎ ሐይቅ የተደበቀ ጸጋ ገልጠናል። በፈለገ ጊዮን ሪዞርት ደግሞ ለባሕርዳር ከተማ እና ለክልላችን ተጨማሪ ጸጋን ደርበናል።
ጎርጎራ፣ ሎጎ ሐይቅ፣ ፈለገ ጊዮን ሪዞርትና ሌሎች ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ስፍራዎች ሲደመሩ የክልላችንን ተጨማሪ ውበትን ይገልጣሉ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ከፍታም ያደምቃሉ።
የክልላችንን ብሎም የኢትዮጵያን የቱሪዝም እድገት የሚያፋጡኑ፣ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ ከቱሪዝም ማግኘት የሚገባንን ሁለንተናዊ ጥቅም እንድናገኝ የሚያደርጉ ናቸው።
እንደዚህ አይነት ሪዞርቶች ለክልላችን ተጨማሪ ጸጋ፤ ለጎብኝዎችም መዳረሻ ኾነው ያገለግላሉ። መንግሥታችን እና ፓርቲያችን ብልጽግና ለቱሪዝም ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
የቱሪዝም ዘርፉን በአግባቡ አልምተን ለመጠቀም መዳረሻዎቻችን እያሰፋን፣ የጥንቶችን እያደስንና እየጠበቅነ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እያለማን እንገኛለን። ይሔንን ተግባር አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል።
ሀገር በትብብር ይገነባል፣ በፈተና በመጽናት የነገውን መልካም መዳረሻ በመመልከት ሀገርን መገንባት ያስፈልጋል። በትብብር ሀገርን የሚያስከብሩ ህዝብን የሚጠቅሙ ለትውልድ የሚተርፉ ሥራዎችን እየሠራን ነው።
በይፋ ሥራ ያስጀመርነው የፈለገ ጊዮን ሪዞርት የትብብራችን ውጤት ነው። ፈለገ ጊዮን ሪዞርት ከሪዞርት ባሻገር ነው። በዚህ ስፍራ መንግሥትና የግል ባለሐብት ተባብረዋል። ሐሳብና ተግባር ተገናኝተዋል፣ ፍላጎት፣ ቦታና ጊዜ ተስማምተዋል።
ስንተባበር ኢትዮጵያን የሚያስጌጡ፣ በብልጽግና ከፍታ ላይ የሚያቆናጥጡ ስራዎችን እንሰራለን። ትብብር ምን ያሕል ሐይል እንዳለው ቀደም ሲል ከታሪካችን አሁን ደግሞ ከእንደዚህ አይነት ስኬቶች ተመልክተናል።
ዛሬም ነገም በትብብር ለትውልድ የሚተላለፍ አሻራ ለማኖር እንሠራለን።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የኢትዮጵያን የአምራች ዘርፍ ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክረውን አራተኛውን ‘ኢትዮጵያ ታምርት’ ኤክስፖ 2018 ዛሬ በይፋ መርቀው ከፍተዋል።