
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 27/2018 (አሚኮ) 85ኛው የኢትዮጵያ የአርበኞች ቀን እየተከበረ ነው። ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትላንቱ በሁሉም መስክ እኔ “ለሀገሬ አርበኛ ነኝ” የሚሉ እና በሥራቸው ሉዓላዊነቷን የሚያስከብሩ አርበኛ ልጆችን አጥብቃ የምትሻ መኾኑን የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ የዛሬው ትውልድ የነገ አርበኝነት ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሐዊ በኸነ መንገድ ወዳጣችው የባሕር በር እንድትደርስ ያለ እረፍት በመሥራት ሊገለጥ ይገባል ብለዋል።
የባሕር በር ለኢትዮጵያ አዲስ ሳይኾን ሀገሪቱ በተፈጥሮ የነበራት እና በታሪካዊ አጋጣሚዎች ያጣችው ሀብቷ መኾኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የባሕር በር የነበራት ሀገር ብትኾንም በተለያዩ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በተደረጉ ሴራዎች ወደ ባሕር በር አልባ ሀገርነት መቀየሯን አስታውሰዋል።
ይህንን ጥያቄ በጦርነት ወይም በኀይል ሳይኾን በሕዝቦች መካከል በሚኖር መግባባት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለመፍታት ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በንቃት እየተከታተለው እንደሚገኝ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር መቆየት እንደማትችል ግንዛቤ እየወሰደ መኾኑ ተገልጿል። “ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር መኖር እንደማትችል ዓለም በሚገባ ተረድቷል”ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድ የሕዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ ረገድ የዘመኑን አርበኝነት ባሳየበት ልክ የባሕር በር ጥያቄም የዚሁ የአርበኝነት አካል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።
ዘጋቢ፦ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !
