
ደሴ: ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር ሴት የብልጽግና ፖርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለፓርቲው የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል። ፖርቲው ለክልል እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረባቸውን እጩዎችንም አስተዋውቋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተሳተፉ ሴቶች እንደተናገሩት ብልጽግና ፓርቲ ሴቶችን በተለያዩ ዘርፎች በማብቃት ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመጀመር እና በማጠናቀቅ የኢትዮጵያን እድገት እያፈጠነ መኾኑንም ተናግረዋል። ሴቶችን በከፍተኛ አመራር ሰጭነት ቦታዎች ላይ በማሳተፍም ቀዳሚ ነው ብለዋል።
ምርጫው በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚሠሩም አስረድተዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ ብልጽግና ፓርቲ የተግባር ፓርቲ መኾኑን ገልጸዋል። ፓርቲው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑንም ተናግረዋል። ፓርቲው የጀመረውን ሀገርን የማልማት ተግባር እንደሚያስቀጥልም አረጋግጠዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው ብለዋል። ፓርቲው ኅብረብሔራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት አደረጃጀቶችን በመፍጠር የራሳቸውን እና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት እየቀየሩ ይገኛሉ ነው ያሉት። ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
