
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት 38 ዓመታት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር የሚያስከብሩ ለሀገራቸው ክብር እና ሉዓላዊነት በቆራጥነት የሚቆሙ የቁርጥ ቀን ልጆችን በማፍራት ስሙ በደመቀ ቀለም ተጽፏል።
አንጋፋው የብርሸለቆ መሠረታዊ ውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የጀግኖች መፈልፈያ ማዕከል ብቻ ሳይኾን የልማት ተምሳሌት ለመኾንም በትጋት እየሠራ ነው።
ትምህርት ቤቱ ከሠራዊት ማሠልጠን ጎን ለጎን ሀገር የቀረጸችውን “በምግብ ራስን የመቻል” ፖሊሲ በተግባር እየሠራበት ይገኛል።
የትምህርት ቤቱ ምክትል አዛዥ ለሥልጠና ኮሎኔል እንዳለ አቤ ለአሚኮ እንደገለጹት በተቋሙ ከ25 ሄክታር በላይ በሚኾን መሬት ላይ ያለውን ጸጋ በመጠቀም ዘርፈ ብዙ የግብርና ልማት ሥራዎችን እየሠራ ነው።
ተቋሙ የራሱን የ”ጥምር ግብርና ዴስክ” በማደራጀት በሰብል ምርት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ላይ ተሰማርቷል። በእንስሳት ርባታ ዘርፍም በወተት፣ በእንቁላል፣ በከብት ማድለብ እና በዶሮ ርባታ ዘርፎች ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ምርቶቹን ለተቋሙ ሠራተኞች ብቻ ሳይኾን ለአካባቢው ማኅበረሰብም እያቀረበ የድርሻውን እየተወጣ ስለመኾኑም ምክትል አዛዡ አስረድተዋል።
እየተከናወኑ ባሉት የልማት ተግባራትም ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች በቋሚ እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ይገኛል።
ዘመናዊ አሠራርን በመከተል እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሥራት በምርትና ምርታማነትም ውጤት እያስመዘገበ ነው። በቀጣይም ከሠራዊት ግንባታው በተጨማሪ የልማት ሥራውንም በስፋት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የሠራዊት ግንባታውን ከልማት ሥራው ጋር አጣምሮ የዘለቀው የብርሸለቆ ጉዞ ለሌሎች ተቋማትም ተምሳሌት የሚኾን ነው።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
#አሚኮ #ኢትዮጵያ #ብርሸለቆ #መከላከያ #ግብርና #ራስን_መቻል
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን
