የዜጎችን የአገልግሎት አሰጣጥ የቀየረው አዲሱ አሠራር!

4

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2018ዐዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ መሶብ አንድ ማዕከል የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ምክትል ከንቲባ አስሜ ብርሌ ተናግረዋል። ማዕከሉ በከተማ አሥተዳደሩ ስር የሚገኙ 10 ተቋማትን እና ሁለት የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን በአንድ ጥላ ሥር አቅፏል።

የሞሰብ አገልግሎቱ ከ72 በላይ አገልግሎቶች እየተሰጡበት እንደኾነ በከተማ አሥተዳደሩ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ወቅት ተገልጿል።
ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ23 ሺህ በላይ ተገልጋዮች ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎትም አግኝተውበታል።

እጅግ ውሥብሥብ እና ፈታኝ የነበረው የመሬት እና የስመ ንብረት ዝውውር አገልግሎት በዲጂታል መንገድ እየተከናወነ እንደኾነ ጠቁመዋል። በጤና ተቋማትም የወረቀት ንክኪ የሌለባቸው አሠራሮች በስፋት ተግባራዊ እየተደረጉ ነውም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም በአንዳንድ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ መሠረታዊ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በቀበሌ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚታዩ የአገልግሎት መጓተቶች፣ ለተገልጋዮች ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ የመስጠት ጉድለት እና ተገቢ ያልኾነ ጥቅም የመፈለግ አባዜዎች አሁንም ትኩረት ይፈልጋሉ ብለዋል።

ተገልጋዮች ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚኾን ወይም የማይኾን ውሳኔን በአጭር ጊዜ እና በግልጽነት የመመለስ ልምድ ገና እንዳልዳበረም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ የከተማ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የዲጂታላይዜሽን ስኬቶችን በማስፋት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የአሠራር ጉድለቶችን ለመቅረፍ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የጣና ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ጌትነት ካሴ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ችግሮች በጊዜ ገደብ ተለይተው ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልም የባለሙያዎችን አፈጻጸም በቅርበት በመገምገም የሕዝብን እርካታ ለማረጋገጥ በትኩረት ይሠራልም ነው ያሉት።

​#BahirDar #ServiceDelivery #MesobCenter #DigitalEthiopia #Amico

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleብልጽግና ፖርቲ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ነው።
Next article“ለሚመጣው ትውልድ ጽኑ፣ በኢንዱስትሪ የበለጸገች እና ራሷን የቻለች ኢትዮጵያን እንገነባለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)